የኢትዮጵያና ሩሲያ መሪዎች ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሩሲያ መሪዎች ተወያዩ
ኢዜአ፤ ጥቅምት 12 /2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ ሶቺ ከተማ ተገናኝተው የሁለቱ አገሮች ትብብር በሚጠናከርበት መንገድ ላይ ተወያዩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሩሲያ ሶቺ ከተማ እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ መድረክ ላይ ለመሳተፍ ትናንት ወደዚያው አቅንተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዚዳንት ፑቲን በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ዙሪያ የመከሩት የሩሲያ አፍሪካ ኢኮኖሚክ መድረክ ዛሬ ከተከፈተ በኋላ ነው። በስፍራው የሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር እንደዘገበው የመሪዎቹ ውይይት ያተኮረው የኢትዮጵያና ሩሲያ ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ ነው። በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለፕሬዚዳት ፑቲን ስለኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚና አጠቃላይ ሪፎርም አብራርተውላቸዋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓመቱ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው "እንኳን ደስ አለዎ" በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያና ሩሲያ በኒውክለር ቴክኖሎጂ አብረው መስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ማዕቀፍ ፈርመዋል። አገሮቹን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያና የሩሲያው የአቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካቼቭ ናቸው። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የኒውክለር ቴክኖሎጂን በጤናው ዘርፍ ለመጠቀም በተለይም ለካንሰር ህክምና እና ለኃይል ልማት ለማዋል ለምታደርገው ጥረት የሩሲያ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል። ድጋፉም በምርምር ዘርፍ የልምድ ልውውጥ ማድረግን ያካተተ መሆኑም ተመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በሩሲያ ቆይታቸው ግዙፍ ከሆኑ የሩሲያ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ይነጋገራሉ። ከእነዚህም መካከል ማዳበሪያ በማምረት የካበተ ልምድ ያለው የአርላችም የተቀናጀ የኬሚካል ማምረቻ እና በማእድን ፍለጋ ሥራ የሚሰራው የጋዝፕሮም ዓለም አቀፍ ኩባንያ ኃላፊዎች ይገኙበታል። ሁለቱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተመልክቷል። በተለይ ጋዝፕሮም ዓለም አቀፍ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል በኃይድሮ ካርቦን ፍለጋ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ኩባንያው በኢትዮጵያ ወርቅ ፍለጋ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ መጠየቁም ይታወቃል። በሩሲያ ሶቺ ከተማ እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ መድረክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በተጨማሪ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ በአህጉሪቱ የሚገኝ የንግድ ማኅበረሰብና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተሳትፈዋል። በሩሲያና በአፍሪካ መካካል ያለውን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነት ማጠናከር የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ ተገልጿል።