''መደመር'' አገራዊ ችግርን በመፍታት ላይ በማተኮር ለውጡ የሚመራበት እሳቤ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
''መደመር'' አገራዊ ችግርን በመፍታት ላይ በማተኮር ለውጡ የሚመራበት እሳቤ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 12/2012 የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ''መደመር'' አስተሳሰብ አገራዊ ችግርን መፍታት ላይ በማተኮር ለውጡ የሚመራበት መንገድ መሆኑ ተገለፀ።
ህብረ-ብሄራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብርና ብልፅግና ደግሞ የመደመር እሳቤ የመጨረሻ ግቦች ናቸው ተብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የተጻፈው ‘መደመር’ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ የነበራትን መጥፎ ታሪክ በመቀየር ከነበሩ ወረቶች በመነሳት ወደ ብልፅግና ማሻገር ላይ ትኩረት አድርጓል።
መፅሃፉ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን የፖለቲካ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ሌሎች በርካታ ችግሮችና ምንጮቻቸውን፤ እንዲሁም ችግሮቹን በማከም ወደፊት መቀጠል የሚቻልባቸውን መንገዶች ያመላክታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምጣኔ ኃብት አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ዕድገት ማስመዝገብ ቢቻልም ዕድገቱ ጥራት እንዳልነበርው ይገልፃሉ።
የዋጋ ንረት፣ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ ዘላቂና አስተማማኝ የስራ ዕድል አለመፈጠርን እንደማሳያ በመጠቆም።
''ድህነትን በመቀነስ የጋራ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያስችል ጥራት ያለው የምጣኔ ኃብት ዕድገት ማረጋገጥ ያስፈልጋል'' የሚሉት አማካሪው ይህ ደግሞ ምርታማነትን በአስተማማኝ ሁኔታ በማሳደግ የወጪ ንግዱን ማጠናከር እንዲሁም ሰፊና አስተማማኝ የስራ ዕድል መፍጠርን ይጠይቃል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የመደመር እሳቤ ቀደም ሲል የተሰበሰቡ ወረቶችን መነሻ በማድረግ በምጣኔ ኃብቱ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቾችን መፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ተናግረዋል።
በመደመር እሳቤ ትብብርና ፉክክር ሚዛን ጠብቀው እንዲሄዱ በማድረግ የምጣኔ ኃብት መረጋጋት እንዲፈጠር ያደርጋል ባይ ናቸው አቶ ማሞ።
የእሳቤው የምጣኔ ኃብት ገጽ ዋና መድረሻ ደግሞ ብልጽግና መሆኑን በማመልከት።
የመደመር እሳቤ ድምር የሰው ልጆች ፍላጎቶችን ታሳቢ ያደረገና ከድጎናማ ከሃብት ክፍፍል ይልቅ ምርታማነትን ማሳደግና የጋራ ብልፅግና ማምጣት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎች ናቸው።
እሳቤው ከዚህ ባለፈ ትምህርትና ጤናን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትና መዋቅራዊ ችግሮች ላይ በማተኮር ለችግሮቹ መፍትሄ እንዲመጣ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር ጌዲዮን ገለጻ፣ የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያ ተኮር የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ትኩረት በማድረግ ከዓለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችና ልምዶች ግብዓት ይወስዳል።
እሳቤው አካታችና ዘርፈ ብዙ ብልጽግናን ግብ ያደረገ ጎራ የለሽ አገራዊ ችግርን ማዕከል ያደረገ እይታ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።
እሳቤው ''የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ችግር ጭቆና ነው'' ብሎ የሚያስቀምጥ ሲሆን ይህም ጭቆና በቀጥታና በመዋቅር የሚካሄድ እንደነበር ያሳያል።
ይህን ጭቆና ለማስቀረት በመግባባት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ መገንባትን በመፍትሄነት ያስቀምጣል።
መደመር የአገረ-መንግስቱን ቅቡልነት ከፍ ለማድረግ እርቀ-ሰላምና ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር የቡድንና የግለሰብ መብትን ያማከለ መፍትሄ ይዞ መቅረቡንም ነው ዶክተር ጌዲዮን ያመለከቱት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህሩ አቶ ዮናስ ዘውዴ ሙሉ-ዕይታ፣ መሰናሰን፣ ግንባታ፣ ተባብሮ መኖር፣ ሚዛን መጠበቅና ስርዓት መፍጠር የመደመር አምዶች ናቸው ይላሉ።
ህብረ-ብሄራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብርና የአገሪቷ ብልጽግና ደግሞ የመደመር እሳቤ የመጨረሻ ግቦች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
ዋልታ ረገጥነት፣ አቅላይነት፣ እምቢተኝነት፣ ሙያን መናቅ፣ ልግመኝነትና አድር ባይነት በእሳቤው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሳንካዎች ይሆናሉ ተብለው እንደሚጠበቁ አቶ ዮናስ አመልክተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ጉዳይ ተንታኙ አቶ መሃመድ ራፊ በበኩላቸው መግባባትና ትብብር፣ ወረትን ማሳደግ፣ ብሄራዊ ጥቅምን ማስከበር፣ ጎረቤት አገራትን ማስቀደም ብሄራዊ ክብርን ማረጋገጥ የመደመር እሳቤ የውጭ ግንኙነት መሰረቶች ናቸው።
አገራዊ ሃይልን ማጎልበት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲን ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ የውጭ ግንኙነት ማስፈጸሚያ ስልቶች ናቸው ብለዋል።