የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና አገር በቀል ዕውቀትን ያካተተ መሆን እንዳለበት ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና አገር በቀል ዕውቀትን ያካተተ መሆን እንዳለበት ተጠቆመ

ጥቅምት 12/2012 ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አደጋ የሆነውን መጠለያ ለማንሳትና ስንጥቁን ለመጠገን የሚደረገው ጥናት አገር በቀል እውቀትን ጭምር ያካተተ መሆን እንዳለበት የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የቅርሱን ጥገና ዘላቂ ለማድረግ የጥናት ቡድኑ በሚያገኛቸው ውጤቶች ዙሪያ ከኅብረተሰቡ ጋር መወያየት ይገባል ተብሏል። ከኢትዮጵያና ከፈረንሳይ የተውጣጡ የቅርስ ጥናትና ጥገና ባለሙያዎች ቡድን ቅርሱን ለመጠገን ሳይንሳዊ ጥናት እያደረጉ ነው። ባለፉት ዓመታት በተለያየ ጊዜ የተደረገው ጥገና ኅብረተሰቡን ያላሳተፈና አገር በቀል እውቀትን ያላካተተ በመሆኑ ዛሬም ከአደጋ አላዳነንም ብለዋል። ቅዱስ ላሊበላ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ በረቀቀ ጥበብ ከአንድ ወጥ አለት ያስፈለፈሏቸው እነዚህ ጥንታዊ የኪነ-ህንጻ ስራዎች አደጋ ተጋርጦባቸዋል። የቤተ መርቆርዮስ ገበዝ ቄሰ ገበዝ አበበ ሲሳይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተጋረጠው አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። በተለይም ይጠና እየተባለ ጥገና ያልተደረገላቸው ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መርቆርዮስና አባ ሊባኖስ ላይ የደረሰባቸው የመሰንጠቅ አደጋ እየተባባሰ ስለሆነ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል። ከ10 ዓመት በፊት እንኳን ያለኅብረተሰቡ እውቅናና ይሁንታ ቅርሱን ከዝናብና ጸሃይ ለመከላከል በሚል የተሰራው መጠለያ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኗል ይላሉ። የቅዱስ ላሊበላና አካባቢው አስጎብኝዎች ማኅበር ፀሀፊ አቶ ካሳሁን አባቡ የጥናት ቡድኑ ሀገር በቀል እውቀትን ለመጠቀም ፍላጎት ማሳየቱ ለቅርሱ ዘላቂ ደህንነት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። የላሊበላና አካባቢው ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ በጎ አድራጎት ማህበር ህዝብ ግንኙነት አቶ ይኼነው መላኩ የቅርሱ ጥገና ሲከናወን ኅብረተሰቡን ያሳተፈ መሆን አለበት ብለዋል። መጠለያውን ለማንሳትና ስንጥቁን ለመጠገን የተሰማሩት የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች ፍጻሜያቸውን ባናውቅም አጀማመራቸው መልካም ነው ይላሉ። "አሁን ያለው መጠለያ አንዱ ብረት ቢወድቅ ቅርሱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናጣዋለን" ይህ ደግሞ ኢትዮጵዊያን ያልተሳተፉበት ስራ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ያሳያል ብለዋል። ከአሁን በፊት በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን ፍጻሜው እንደ ጅማሬው አያምርም፤ ይህ መቀጠል የለበትም ብለዋል። የቅዱስ ላሊበላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ወልደሚካኤል ቀደም ሲል የነበረው ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት አሰራር አይቀጥልም ብለዋል። በቀጣይ የኅብረተሰቡን ተሳትፎና ባለቤትነት ለማረጋገጥ የጥናት ቡድኑ የደረሰበት ውጤት በአማርኛ ቋንቋ ጭምር ተተርጉሞ ለኅብረተሰቡ እንደሚቀርብ ገልጸዋል። ለቅርሱ ጥበቃ ከሚወጣው ወጭ በተለያዩ አካላት በሰበብ የሚወጣው ይበልጥ እንደነበር መገምገማቸውን ጠቁመው፤ ግልጽነት ተጠያቂነት የጎደለው የገንዘብ አጠቃቀም ስርዓት እንዳይኖር ቁጥጥር እናደርጋለን ብለዋል።