ቀጥታ፡

የሁለተኛ ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር በ4 ሺህ 500 ጤና ኬላዎች ተግባራዊ ይደረጋል

ጥቅምት 12/2012 የሁለተኛ ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር በተያዘው በጀት ዓመት በመላው አገሪቱ በተመረጡ 4 ሺህ 500 ጤና ኬላዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። በመላው ኢትዮጵያ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ በተተገበረው መርሃ ግብሩ መሰረትም በተለይ የእናቶችና ህጻናት ሞትን፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን፣ ቲቢንና የወባ በሽታን በመቀነስ ረገድ ውጤት ማስመዝገቡን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቀየሰው የምዕት ዓመቱ የልማት ግቦች መሰረት  የተቀመጠውን የጤና ልማት ለማሳካት የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩ ቁልፍ ሚና መጫወቱንም  ሚኒስቴሩ ያመለክታል። አገሪቱ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት የተጠናቀቀውን የምዕተ ዓመቱን የጤና ግብ ያሳካችው ከተቀመጠለት የትግበራ ጊዜ ሁለት ዓመት ቀድማ መሆኑም ይነገራል። የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት በ1 ሺህ 600 የጤና ኬላዎች የሙከራ ስራው የተጀመረው ሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር በተያዘው ዓመት በሰፊው ሥራ ላይ ይውላል። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር እስከ 2030 የሚተገበረውን ዓለም አቀፍ ዘላቂ ልማት ግብ ለማሳካት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ላይ ብቻ በማተኮር ውጤት ማስመዝገብ እንደማይቻል ነው ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። የአገሪቱ  የበሽታ ዓይነት ከመቀየርና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የጤናውን ዘርፍ ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ በማመን የጤና አገልግሎቱንና ተደራሽነቱን ለማስፋት ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በተለይም የምእተ ዓመቱን የልማት ግብ የተካውን የዘላቂ ልማት ግብ ለማሳካት ጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩ መሳኝ ነው ብለዋል። ሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ቀድሞ ከነበረው አገልግሎት በተጨማሪ በአገሪቱ አሳሳቢ ችግር እየሆኑ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል ትኩረት ይሰጣል ብለዋል። ቀድሞ በ16 ፓኬጅ ሲሰራ የነበረውን የመርሃ ግብር ወደ 18 በማሳደግ የጤናውን አገልግሎት በጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል እንደሚሰራ በማከል። የኩላሊት፣ የካንሰር፣  የስኳርና የአእምሮ ህመሞችን ከማከም ባሻገር አስቀድሞ የመከላከል ተግባርም በመርሃ ግብሩ የተካተቱት አዲሶቹ ፓኬጆች የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል። ሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽ መርሃ ግብር በዋናነት የሚተገበረው የጤና ኬላዎችን አገልግሎት በማሳደግ፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል። ሁለተኛው ትውልድ መርሃ ግብሩ በመጪዎቹ አስር ዓመታት  ሙሉ በመሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ይደረጋል። የተሻለ በጀት ከተገኘ መርሃ ግብሩን ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለመጨረስ ከክልሎች፣ ከወረዳዎችና ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም