መገናኛ ብዙኃን በአገራዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው እይታ እየጠበበ መጥቷል፡- አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን በአገራዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው እይታ እየጠበበ መጥቷል፡- አስተያየት ሰጪዎች
አዲስ አበባ ጥቅምት 12 /2012 መገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጯቸው መረጃዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው እይታ እየጠበበ መምጣቱን የሚያመለክቱ መሆናቸውን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። ተቋማቱ የተጣለባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት ጉዳይን እየዘነጉ መሆናቸውንም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት። ከጋሞ የመጡት የሐይማኖት መሪ አቶ ዋንቱ ባና እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር እንደመሆኗ መጠን ህዝቦች በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ለዘመናት ተቻችለው ኖረዋል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ መረጃዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው እይታ እየጠበበ መምጣቱን ገልጸዋል። በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው እይታ እንዲጠብ ያደረጋቸው ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በመዘንጋትና የራስን ፍላጎት በማስቀደም እንደሆነም አስረድተዋል። ኡዝታዝ ሳዲቅ ወጌቦ በበኩላቸው፤ በአገሪቷ በመጣው ለውጥ የኤሌክትሮኒክስና የህትመት መገናኛ ብዙኃን በነጻነት ሀሳባቸውን እንዲያንጸባርቁ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመዋል። አገራዊ ለውጡ ያመጣውን ዕድል በመጠቀም ተገቢውን መረጃ ለህዝብ ማሰራጨት ተገቢ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ኡዝታዝ ሳዴቅ፤ ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጭ የሚችሉ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ማሰራጨታቸው ለአገሪቷ ህልውና ከባድ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። መጋቢ ፀጋዬ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን የተጣለባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት ከፍተኛ ቢሆንም ሙያው በሚጠይቀው ስነ-ምግባር ልክ እየሰሩ አለመሆኑን ተናግረዋል። እንደ መጋቢ ፀጋዬ ገለጻ፤ ለህዝቡ የተሳሳተ መረጃ ከማሰራጨታቸው በፊት ከመረጃ ምንጮቹ የሚመጣው መረጃ እውነተኛ መሆኑን የማጣራት ሙያዊ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ትንታኔ የሚሰጡ ምሁራንም እውቀታቸውን ተጠቅመው የአገሪቱን መልካም እሴት በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ከማድረግ ባለፈ የራሳቸውን አፍራሽ አጀንዳ ማራመድ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙኃን የተጣለባቸው ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው አንዱን ወገን ከፍ አንዱን ወገን ደግሞ ዝቅ የሚያደርጉ አሉ። ባለስልጣኑ ክትትልና ቁጥጥሩን በማጠናከር በተቋማቱ ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መገናኛ ብዙኃንን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ''ባለፉት ዓመታት መገናኛ ብዙኃን ነጻ የመሆን ፍላጎት ነበራቸው ነፃ ለመሆንም ጥያቄ አቅርበው ነበር'' ብለዋል። አብዛኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን ነፃ ለመሆን ባቀረቡት ጥያቄ ልክ ነፃ ሆነው እየሠሩ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ለኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ ከመስራት ይልቅ የዘር፣ የሐይማኖት እና የገንዘብ ነጋዴዎች በመሆን እየቀለዱና የሆነ አካልን ወክያለሁ ብለው በሚነግዱ ሰዎች እጅ መውደቃቸውን ተናግረዋል። "ለእነዚህ ነጋዴዎች ሕዝቡ ዓይንና ጆሮ ባለመስጠት ሊቀጣቸው ይገባል" ሲሉም መክረዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም ሕጉን መሠረት በማድረግ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሳስበዋል።