ፖሊስ አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ በፖሊስ እርምጃ ተወሰደብኝ በሚል ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት ነው አለ

ጥቅምት 12/2012 አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ በፖሊስ እርምጃ ተወሰደብኝ በሚል ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬ ረፋድ ላይ መንገድ የመዝጋትና ረብሻ የማስነሳት ህገ-ወጥ ተግባር ተስተውሏል። ለተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች አክቲቪስት ጀዋር መሐመር ለተከታዮቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው "ልታሰር ነው፣ ጥቃት ሊደርስብኝ ነው" የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸው ለተቀሰቀሰው የጸጥታ ችግር ምክንያት መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል። በዚህም መንግስትም ሆነ በፖሊስ የተወሰደ ምንም አይነት እርምጃ አለመኖሩንና የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው። ኮሚሽነሩ እንዳሻው ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ፖሊስ ለውጡን ተከትሎ ወደ አገር የገቡ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች በሚኖሩበት አካባቢና በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ችግር እንዳያጋጥማቸው የጥበቃ ከለላ ሲያደርግ ቆይቷል። አገሪቱ ላይ ይንጸባረቁ የነበሩ የተለያዩ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈቱ ሰላማዊ ሁኔታ እየተረጋገጠ በመምጣቱ እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በሰላም ተንቀሳቅሰው መኖር የሚችሉ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የግል ጥበቃዎችን የማንሳት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም አውስተዋል። አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ በፖሊስ እርምጃ ተወሰደብኝ በሚል ያስተላለፉት መልዕክት ስህተት መሆኑንና ምንም አይነት የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በመሆኑም ወጣቶችና አጠቃላይ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ከሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተጋገዝ የተዘጉ መንገዶችን እንዲከፈቱና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማገዝ አለበት ሲሉም ተናግረዋል። ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በመቆጣጠር የሰላምና የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የራሱን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። ኮሚሽኑ በህግ ማስከበር ሂደት ውስጥ ችግሮች እንዳይፈጠሩና የህብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ሰላምን የማስጠበቅና ህግን የማስከበር ስራውን እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም