ቀጥታ፡

የጀርመን መንግስት የ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እርዳታ ሰጠ

ኢዜአ፤ጥቅምት 12/2012 የጀርመን መንግስት በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉን ለማገዝ የሚያስችል የ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እርዳታ ሰጠ። የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱን  ዛሬ በአዲስ አበባ የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የጀርመን አባሳደር ብሪታ ዋግነር ናቸው። ሚኒስትር ዲኤታው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የጀርመን መንግስት የለገሰው የ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እርዳታ ግብርናውን ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ያስችላል። ከዚህም ሌላ ድጋፉ ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠር፣ ከስደት ተመላሾችን ለማገዝ እንዲሁም በግጭቶች ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ለማቋቋም እንደሚውልም ነው የገለጹት። ጀርመን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የድጋፍ መጠን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያሳደገች ነው ብለዋል። በቅርቡም በአገሪቱ የሚደረገውን ለውጥ ለማገዝ የ100 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል መግባቷንም አስታውሰዋል። ይህንን ቃል ኪዳን ወደ ተግባር ለመለወጥ በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት። በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሪታ ዋግነር በበኩላቸው የጀርመን መንግስት ኢትዮጵያ እያካሔደች ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማገዝ ቁርጠኛ አቋም አለው። በዚህም መሰረት ጀርመን በኢትዮጵያ የሚካሔደውን ለወጥ የማገዝ ተግባሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል። በዛሬው እለት የተደረገው ድጋፍም ጀርመን በቋሚነት ለኢትዮጵያ ከምታደረገው ድጋፍ ተጨማሪ እገዛ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም