ቀጥታ፡

የቡና ልማትን ለማሳደግ በዘርፉ ከተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ለመስራት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ሊሆን ነው

አዲስ አበባ  ጥቅምት 11/2012 በኢትዮጵያ የቡና ልማትን ለማሳደግ በዘርፉ ከተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ለመስራት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቡና አምራችነቷ ከዓለም አቀፍ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የቡና መገኛ አገር እንደመሆኗና ከምርቷም ተፈላጊነት አንጻር ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ እየሆነች እንዳልሆነ ይነገራል። በተጨማሪም ከ13 አመታት ወዲህ በአለም ገበያ ላይ እየታየ ያለው የቡና ዋጋ መውረድና መቀዛቀዝ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል ተብለዋል። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ "በኢትዮጵያ ቡና ላይ ከዚህ ቀደም እሴት ጨምሮ በመላክ ረገድ በአዋጅም በደንብም የተገለጸ ነገር አልነበረም"። ይሁንና በእድገትና ትራንስፎርሜሽን የተያዘውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም በቡናው ዘርፍ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ በተገቢው ሁኔታ ለማመንጨትና በዘርፉ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ገቢና ኑሮ ለመለወጥ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ከእነዚህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የቡና እደሳ ስራ፣ የቡና እንክብካቤ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራዎች፣ የተጓዳኝ ሰብሎች ልማት፣ የደጋፊ መስኖ ልማት እንዲሁም የሰብል በሽታና ተባይ ቁጥጥርና መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ውጤታማና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች እና የግብአት አቅርቦት ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ግብይቱንም ፍትሄዊና አስተማማኝ ለማድረግ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት። በአሁኑ ሰዓት ቡናን እሴትን ጨምሮ ወደተለያዩ አገራት መላክ በሚያስችል መልኩ በደንብና መመሪያዎች ላይ በማካተት በተለይም የኢንደስትሪ ዞኖችን የቡና እሴት የሚጨመሩበትን ሁኔታዎች የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በዘርፉ የተሰማሩ የተለያዩ አገራት ኢንቨስተሮችን ወደ አገር ወስጥ በመጋበዝም ከአርሶ አደሮችና አቅራቢዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል። በዚህም በቡና ኢንደስትሪ ውስጥ የተሰማሩ የውጭ አገር አካላትን እንዲሁም የአገር ወስጥ አምራቾችና ላኪዎችን በሽርክና ማህበር አብረው እንዲሰሩና ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያግዝ አሰራርም ከዚህ አመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሰባት እስከ አስር በመቶ የሚሆን ቡና ለአለም ገበያ በማቅረብ ላይ እንደምትገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም