ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ፍቃድ አሰጣጥ ማዕቀፍ አዘጋጀ

አዲስ አበባ  ጥቅምት 11/2012የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ፍቃድ አሰጣጥ ማዕቀፍ ማዘጋጃቱን ገለጸ። ባለሥልጣኑ ከተቋቋመ አንስቶ ባከናወናቸው ተግባራትና እያከናወኗቸው ባሉ ስራዎች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ በሰጡት መግለጫ፤ ባለሥልጣኑ በዚህ ዓመት ከሚያከናውናቸው ስራዎች መካከል አንዱ ለሁለት ዓለም አቀፍ ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ፍቃድ መስጠት መሆኑን አስታውቀዋል። ፍቃድ ከመስጠቱ በፊትም ፍቃድ አሰጣጡ የሚመራበት ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ማዕቀፉ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ማዕቀፉም ለህዝብ አስተያየት ክፍት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በባለሥልጣኑ ድረ ገጽ http://www.eca.et ላይ ማንኛውም ፍላጎት ያለው አካል በመግባት በሰነዱ ላይ ግብዓት መስጠት ይችላል ብለዋል። እንደ ኢንጂነር ባልቻ ገለጻ የተሰጡ አስተያyቶችን በመያዝም ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ መድረክ በማካሄድ ተጨማሪ ማብራሪያዎችም ይሰጣሉ። ባለስልጣኑ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ፈቃድ ይሰጣል፣ ይቆጣጠራል። በተለይም የአገልግሎት ታሪፍ ላይ ቁጥጥር ማድረግ፣ የቁጥር፣ የሞገድ፣ የዶሜይን ስም እና አይ ፒ አድራሻ የማሳሰሉትን ያስተዳድራል። እንዲሁም የቴክኒክ ደረጃዎችን ማውጣት፣ በአገልግሎት ደረጃም ሆነ በመሳሪያ ደረጃ ወደ እዚህ አገር የሚገቡ ማንኛውም ለኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሚውሉ መሳሪያዎች ላይ ደረጃ ማውጣትም ለባልሥልጣኑ የተሰጡ ኃላፊነቶች ናቸው።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም