ቀጥታ፡

የኢህአዴግ ውህደት በአማራጭ ይፈጸማል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 11/2012 ኢህአዴግን የማዋሃዱ ጥናት በአማራጮች ለመፈጸም ትኩረት ተድርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የምክር ቤቱ አባላት ለሚያነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው። በምላሻቸውም ኢህአዴግን የማዋሃድ አጀንዳ ላለፉት አምስትና አስርተ ዓመታት ሲሰራበት ቆይቷል ብለዋል። በተለያዩ ጉባኤዎችም አጀንዳው ሲነሳ መቆየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም በሀዋሳው የኢህአዴግ 11ኛው ጉባኤ ምልዓተ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ አጀንዳውን ማጽደቁን አስታውሰዋል። እንዲያውም በጉባኤው ከሚቀጥለው ጉባዔ ከመምጣቱ በፊት የኢህአዴግ ምክር ቤት የመዋሃዱን ሥራ ካጠናቀቀ ውህደቱን ለመፈጸም ሥመምነት ተደርሶ አንደነበርም ገልጸዋል። በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት ውይይትና ምክክር ላይ በመሆኑና ያልተቋጨ ጉዳይ በመሆኑ በቅርቡ ውሳኔው ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል። በጥናቱ መሰረትም ኢህአዴግ "በምን መልኩ" ውህደቱን መፈጸም እንዳለበት በተመለከተም አማራጭ መቀመጡን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍንጭ የሰጡት። ውህደቱን በተመለከተ እስከሁን በኢህአዴግ ውስጥ አያስፈልግም የሚል እምነት ያለው ያለም ብለው ነገር ግን "አሁን ጊዜው አይደለም የሚሉ አሉ" ብለዋል። ያም ሆኖ ለውይይትና ለምክክር ክፍት መሆኑን ጠቁመው የውህደት ውሳኔውም ምክር ቤቱ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ነው የተናገሩት። ፓርቲው ስያሜ ሲቀይር የፓርቲው ህጋዊነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ግለሰቦችም ስህተት መሆናቸውንና ምንም አይነት የቅቡልነት ጥያቄ እንደማያስነሳ ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ ፓርቲ ሆነው "እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ አትኖርም" የሚለው እሳቤ በመሰረታዊነት ስህተት መሆኑን አስምረውበታል። እንደ እርሳቸው ገለጻ "እኛ ከሌለን አገር የለም፣ እኛ ከሌለን መንግሥት የለም የሚባለው ነገር ስህተት ነው" ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ እሳቤ ሳይኖር ኢትዮጵያ ነበረች" በማለት ተናግረዋል። "ኢትዮጵያ የኢህአዴግ አባት እንጂ፤ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም"  በማለትም ኃሳባቸውን አጠናክረዋል። ያም ሆኖ ውህደቱ አንድነትና ሰላም ለማምጣት አንደሚያስችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም