ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ሽልማት ተበረከተለት

ጥቅምት 11/2012 በኳታር ዶሃ በተካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተለት። በሻምፒዮናው ላይ ውጤት ላመጡና ተሳትፎ ላደረጉ አትሌቶችና አጠቃላይ የልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን በኤሊያና ሆቴል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጋራ የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል። ከዚህ ሽልማት በተጨማሪም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የስፖርት ኮሚሽን ለልዑካን ቡድኑ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ከመስከረም 16 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2 ወርቅ 5 የብር እና 1 የነሐስ በድምሩ በዘጠኝ ሜዳሊያ አምስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በዚህ ሽልማት 1 ሚሊዮን 160 ሺህ ብር፤ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ደግሞ  580 ሺህ በድምሩ 1 ሚሊዮን 740 ሺህ ብር ለልዑካን ቡድኑ ተበርክቷል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሀብታሙ ሲሳይ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዶሃ የነበረውን ሙቀቱንና አስቸጋሪ  ሁኔታን ተቋቁመው ያስመዘገቡት ውጤት ሊደነቅ የሚገባው ነው ብለዋል። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈውና የነበረውን ጫና ተቋቁመው የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ አትሌቶች ክብር እንደሚገባቸው ገልጸዋል። እ.አ.አ በ2020 ለሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድርም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባና መንግስትም ለዚሁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል። የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው በሻምፒዮናው የተገኘው ድል ከውጤቱ ባለፈ የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ የተዋወቀበት እንደሆነ አክለዋል። "አትሌቶቻችን ያስለመዱንን ውጤት በሻምፒዮናው እንድናገኝ አድርገውናል" ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮችም "ከአትሌቶቻችን ብዙ እንጠብቃለን" ብለዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አስፈሪና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አትሌቶቹ ያደረጉት ተጋድሎ እጅጉን እኩሪ እንደሆነ ገልጻለች። ሽልማቱ የዕለት ተዕለት ልፋታችሁንና ጥረታችሁን የሚመጥን ባይሆንም የእናት አገራችሁን አደራ ተቀብላችሁ ላስመዘገባችሁት ውጤት እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ ነውም ብላለች። "የወርቅ ሜዳሊያ እናገኝባቸዋለን ባልናቸው ውድድሮች ውጤት ባናመጣም የዶሃ ቆይታችን ትልቅ ትምህርት ያገኘንበት ነው" ብላለች። አትሌቶች የሚያገኙት ሽልማት አሁን ካለበት እንዲሻሻል የሚያደርቅ ረቂቅ መመሪያ እንደተዘጋጀና ፌዴሬሽኑ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርቦ እንደሚጸድቅም ነው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የገለጸችው። በዶሃ ከውድድሩ በተጨማሪ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ለአትሌቲክሱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ 'ቬተራን ፒን' የሚል ስያሜ ያለው ሽልማት እንዳበረከተም አውስታለች። አቶ ዱቤ ሽልማቱን ያገኙ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን በመግለጽ። በተጨማሪም ማህበሩ ለቀድሞ የረዥምና መካከለኛ ርቀት አሰልጣኝ ወልደ መስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) በዓለም ላይ ከሚገኙ ሰባት የአትሌቲክስ አሰልጣኞች አንዱ በማለት እውቅና እንደሰጣቸውም አክላለች። ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በህዳር ወር 2012 ዓ.ም በሚያደርገው ስብሰባም የታዋቂ አትሌቶች መገኛ ለሆነችው አርሲ/ቦቆጂ/ ምርጥ የአትሌቶች መፍለቂያ በሚል ሽልማት ለመስጠት ቃል መግባቱንም ጠቁማለች። በቀጣይም እ.አ.አ በ2020 በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለሚካሄደው ውድደር ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርግም አክላለች። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስም ኮሚቴው እ.አ.አ በ2020 በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር እቅድ ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። አትሌቲክሱም የ10 ወር ለሚቀረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከወዲሁ ዝግጅቱን እንዲያደርግ ኦሎምፒክ ኮሚቴው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። ቶኪዮ ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት ሞቃታማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖርና የዶሃውን ተሞክሮ በመውሰድ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር የሚካሄድበት ቦታ መቀየሩንና ይህም የሆነበት ምክንያት በወቅቱ የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በሽልማት ስነ ስርአቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የወርቅ ሜዳሊያ ላገኙ የ40 ሺህ የብር ሜዳሊያ ላገኙ የ30 ሺህ ለነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች 20 ሺህ ብር፣ ዲፕሎማ ላመጡ 10 ሺህ እንዲሁም ተሳትፎ ላደረጉ አትሌቶች 5 ሺህ ብር ሽልማት ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ የወርቅ ሜዳሊያ ላገኙ የ20 ሺህ፣ የብር ሜዳሊያ ላገኙ የ15 ሺህ ብር፣ የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡ 10 ሺህ፣ ዲፕሎማ ላመጡ 5 ሺህ፣ ተሳትፎ ላደረጉ 2 ሺህ 500 ብር ሽልማት ሰጥቷል። በሽልማት ስነ ስርአቱ ወቅት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የስፖርት ኮሚሽን በቀጣይ ለአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም