ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከፈረንሳይ  ፕሬዚዳንት  ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያዩ

57
ኢዜአ፤ ጥቅምት 11/2012 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከፈረንሳይ  ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፖሪስ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ውይይታቸው በሁለትዮሽ ግንኙነት እና በዘርፈ ብዙ ትብብር ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በተለይ በሃገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር በትኩረት ለማሻሻል መግባባት ላይ ደርሰዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ትላንት በፓሪስ ከተማ የኢትዮፈረንሳይ ቢዝነስ ፎረም የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ሃገር፤  የብዝሃነት መኖሪያ እና የኢንቨስትመንት ተመራጭ   መዳረሻ መሆኗን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እና ሁሉን አቀፍ ዕድገት በፍጥነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የሪፎርም ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኗንም አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ትብብር የበለጠ ሊጎለብት የሚችለው በንግድ እና በኢንቨስትመንት  መደገፍ ሲቻል መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በዚሁ ወቅት አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጭ ባለሃብቶች የተመቸ የኢንቨስትመንት ድባብ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በፎረሙ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ባለሃብቶች የሁለቱን  ሀገራት ትብብር በንግድ እና በኢቨስትመንት ትስስር እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በጣሊያን እና በፈረንሳይ የነበራቸውን የውጭ ሃገር የስራ ተልዕኮ አጠናቀው ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።(ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት)  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም