በዋግህምራ ብሄረሰብ ለተቸገሩ ወጎኖችን የሚቀረብ የምግብ እህል እየተጓጓዘ ነው

61
ጥቅምት 10/2012 በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ድርቅ ባስከተለው ችግር ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት የምግብ እህል እየተጓጓዘ መሆኑን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ  አቶ መልካሙ ደስታ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በዞኑ ከክረምቱ ዝናብ መዛባት ጋር ተያይዞ ባጋጠመው ድርቅ  126 ሺህ በላይ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ድርቁም በሰሃላና በዝቋላ ወረዳዎች ቢጎላም በቀሩት አምስት ወረዳዎች በከፊል መከሰቱን ተናግረዋል። ለችግር የተጋለጡት እነዚህ ወገኖችን ለመታደግ ከክልሉ  መንግስት ጋር በመነጋገር ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ስንዴ፣ ዘይትና ክክ  ማጓጓዝ መጀመሩን አስታውቀዋል። በቅርብ ቀናትም ማከፋፈሉ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። በተጨማሪም ከ65 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት መኖ ፍለጋ  ከወረዳ ወደ ወረዳ መሰደዳቸውንም ጠቁመዋል። "መንግስት በድርቁ ምክንያት በሰው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል" ያሉት ኃላፊው ያጋጠመውን የእንስሳት መኖ እጥረት  በተመለከተም አርሶአደሩ የእንስሳት ቁጥሩን እንዲቀንስ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። በዞኑ የተከሰተዉ ድርቅ ተከትሎ በሰው እና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል ከጽህፈት ቤቱ እውቅና ውጭ በማህበራዊ ሚሚያ ገንዘብ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ሆኖም  ከመንግስት አቅም በላይ ባለመሆኑም  ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም አካል በጽህፈት ቤቱ በኩል ብቻ ማድረግ እንደሚችል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም