ቀጥታ፡

ስዊድን ለኢትዮጵያ ምርጫና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመደገፍ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 10/2012 ስዊድን በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለሚካሄደው ምርጫና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመደገፍ ከ4ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ልታደርግ መሆኑ ተገለጸ። የገንዘብ ሚኒስትር ዴታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ቶርብዮን ፔተርሰን የ4 ሚሊዮን 679 ሺህ 901 ዶላር የድጋፍ ስምምነቱን ዛሬ በሚኒስቴሩ ተፈራርመዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዮናስ ምትኩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሚደረገው ድጋፍ በ2012 ዓ.ም በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ለሚደረገው እንቅስቃሴና የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው። የገንዘብ ድጋፉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እ.አ.አ ከ2019 እስከ 2022 "ምርጫዎችን በመደገፍ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መጠናከር" በሚል በኢትዮጵያ ለሚተገብረው ፕሮጀክት የሚውል እንደሆነ ተናግረዋል። ''በፕሮጀክቱ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማት አቅምን በማጎልበት ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ የማድረግ ስራ ይሰራል'' ብለዋል። በዴሞክራሲ ተቋማት ተጠያቂነት እንዲሰፍን የህዝብ ተሳትፎና የህዝብ ውክልና እንዲያድግ እንዲሁም የጾታ እኩልነት እንዲኖር አቅማቸውን የመገንባት ስራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ዋና ኦዲተር በፕሮጀክቱ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ከሚደረጉ የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል እንደሚገኙበት አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም