በመዲናዋ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ሊያመላክት የሚችል ግብረኃይል ተቋቋመ

97
ጥቅምት 10/2012 በአዲስ አበባ ከተማ የወሳኝ ኩነት አገልግሎትን በማዘመን ሂደት ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን መንስኤ የሚያጣራ ግብረኃይል ተቋቋመ። ግብረ ኃይሉ ከከተማዋ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ኤጀንሲ፣ ከኢትዮ-ቴሌኮምና ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በተውጣጡ ባለሙያዎች የሚዋቀር መሆኑም ተገልጿል። በወሳኝ ኩነት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በነዋሪዎች የሚነሱ ቅሬታዎች ይስተዋላሉ። የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ እየገጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ተወያይቷል። በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው የአይሲቲ ዳይሬክተር አቶ አዕምሮ ካሳ እንዳሉት ኤጀንሲው አገልግሎቱን ዘመናዊ ለማድረግ ባለፉት አመታት ብዙ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮም የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎትን በዲጂታል አሰራር አስደግፎ መስጠት መጀመሩንና እስካሁን ባለው ሂደትም ከ60 በላይ ወረዳዎች ይህን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አንስተዋል። የባለሙያና የግብዓት እጥረት እንዲሁም ተያያዠ  ችግሮች አገልግሎቱን ወደሌሎች ወረዳዎች እንዳያሰፋ ማድረጉን ግን አልሸሸጉም። የዲጂታል አገልግሎቱን እየሰጡ ባሉ ወረዳዎችም ነዋሪዎች በአግባቡ እየተስተናገድን አይደለም የሚል ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን አንስተው ለዚህም ምክንያት የሆኑት የኔትወርክ በሚፈለገው ፍጥነት አለመኖርና ብልሽት ሲገጥም በአፋጣኝ ምላሽ አለማግኘት ምክንያቶች መሆኑን ያነሳሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የራስ አቅምን የመገንባት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም ተባብረው የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። በዛሬው ውይይትም የችግሩን መንስኤ የሚያጠናና መፍትሄ ለመጠቆም የሚረዱ ሃሳቦችን የሚጠቁም ግብረ ኃይል መቋቋሙን አንስተዋል። ኤጀንሲው ኀብረተሰቡ እንዳይጉላላ በየወረዳው ችግር ሲገጥም ሊፈቱ የሚችሉ የአይሲቲ ባለሙያዎችን ቁጥር የማሳደግ ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። በቀጣይም አገልግሎቱን ለብቻው ሊሰጥበት የሚችልበት የራሱ መስመር (ቪ ፒ ኤን አድራሻ ) እንዲኖረው በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መታቀዱን አስረድተዋል። ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ የአይሲቲ ዳይሬክቶሬት የመጡት አቶ ይግረም ማሞ በበኩላቸው ወደ ኤጀንሲው ከሚመጡ ጥያቄዎች ውስጥ በወሳኝ ኩነት ላይ ለሚመጡት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። አሁንም በግብረ ኃይሉ ውስጥ የኤጀንሲው ባለሙያዎች ተሳትፈው ችግሩን ለመለየትና የሚመለከታቸውንም በመውሰድ ለመፍታት እንደሚሰሩ አስረድተዋል። የኢትዮ-ቴሌኮም የኢንተርፕራይዝ ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር  አቶ ፍስሃ መንግስቱ በበኩላቸው ተቋማቸው ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት መፍትሄ ይሰጣል ብለዋል። ሆኖም ወሳኝ ኩነት ለመሰሉ ተቋማት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም ከኬብል ስርቆት ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ለአገልግሎት መቆራረጥ መንስኤ እየሆነ መሆኑን አስረድተዋል። ይህንን ችግር ለመፍታትም ከፀጥታ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ከተቋማት ጋርም በሚገጥሟቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር ችግሮቹ እየተፈቱ መሆናቸውና በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ግብረ ኃይሉም ከኔትወርክ ጋር ተያይዞ እየገጠሙ ያሉ ችግሮች በምን ምክንያት እንደመጡና በማን እንደሚፈቱ ለመለየት እንደሚረዳም ተናግረዋል። ኢትዮ-ቴሌኮም ሊፈታ የሚችላቸውን ጉዳዮች ለመፍታት በሌሎቹም ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም በማከል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም