በአገሪቱ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል -ምሁራን
ጥቅምት 10/2012 በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ማህበረሰቡ ለዘመናት ያዳበራቸውን ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ፡፡ “የኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ዳሰሳ ለሰላምና ልማት እድገት” በሚል መሪ ቃል በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው 5ኛው አገር አቀፍ የባህልና ኪነ ጥበብ አውደ ጥናት ላይ ከ15 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል፡፡ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ-ጹህፍ መምህርና የግጭት አፈታት ተመራማሪ ዶክተር ገብረየሱስ ተክሉ "ለአንድነትና ሰላም አክራሪ ብሄርተኝነት ወይስ ባህላዊ እሴት ማጎልበት" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች የሚተርፍ ታሪክ፣ ባህልና እሴቶች ባለቤት ናት፡፡ ምንም እንኳ አገሪቱ የታሪክና የባህል ጸጋዎች ባለቤት ብትሆንም አሁን ላይ በአጉል መጤ ባህል እየተበረዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አባቶች ለዘመናት ያደበሩት የአብሮነትና የመቻቻል እሴት እየተረሳ በመምጣቱ ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች ጸጋዎች የአገር ኩራት መሆናቸው ቀርቶ የልዩነትና አለመግባባት መፈጠር ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በሁለንተናዊ ተዛምዷቸው ከፍተኛ በሆኑት በትግራይና አማራ ክልሎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በአባቶች ሽምግልናና በሀይማኖት አባቶች ውይይት ከመፍታት ይልቅ በመግለጫ ጋጋታ፣ በፉከራ፣ በዛቻና በእልህ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተገቢነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ በተለይ ''በሁለቱ ክልሎች ባደረኩት ዳሰሳ ህብረተሰቡ ላይለያይ በደም የተጋመደና የተዋለደ በመሆኑ መለያየትን ሳይሆን አንድነትንና አብሮነትን አብዝቶ የሚናፍቅ እንጅ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ለጦርነት የሚዘጋጅ ስነ ልቦናና ፍላጎት የለውም'' ብለዋል፡፡ በመሆኑም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እኔ የበላይ አንተ የበታች በሚል የተሳሳተ ትርክት የሚነሳዉን የጸጥታ ችግር በባህላዊ ግጭት አፈታት ዘዴ በመፍታት የአገሪቱን ሰላምና አንድነት መመለስ እንደሚቻል በጥናታቸው አለመላክተዋል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጅ መምህርና የሰላምና ልማት ተመራማሪ አቶ ጉባይ አሳዬ "ጥቁር ደም" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት በአማራ ክልል ደም አንመልሳለን እየተባለ በፉክክር የሚቀጥለው የመገዳደል ስሜት ኋላቀርነትን የሚያመላክት ነው። በቂም በቀል የሚካሄድ መገዳደልን ለማስቀረት በአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች የሚካሄደው እርቅ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መሰረት በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል። በኢትዮጵያ ያሉ አቀር በቀል እውቀቶችን በጥናት በመለየትና በማጎልበት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰሩ መሆናቸዉን የተናገሩት ደግሞ የአገር በቀል እውቀቶች ጥናትና ምርምር ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልፈታ አብደላ ናቸው፡፡ ''ከ130 በላይ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ቢኖሩም በግንዛቤ እጥረትና በቸልተኝነት ስራ ላይ እንዲውሉ ባለመደረጉ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመጋባባቶች መፍታት አልተቻለም'' ብለዋል፡፡ ከባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ወስጥም 10ሩን በማጥናት በመጽሐፍ መልኩ ታትመው የወጡ ሲሆን 45 የሚሆኑት ደግሞ በመጠናት ላይ መሆናቸው አመልክተዋል። በሰላም ሚኒስቴር የሰላም እሴቶች ግንባታ ባለሙያ አቶ ትዕዛዙ ደለለዉ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በጥናት የተደገፉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ተጠቅሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንም ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና የሐይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የህግ ማቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደዉ አዉደ ጥናት ላይ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተወካዮች መሳተፋቸው ታውቋል።