የግብርና ምርምር ውጤቶችን በቴክኖሎጂ በማገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ጥቅምት 9/2012  ከተለያዩ የምርምር ተቋማት የሚወጡ የምርምር ውጤቶችን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማስተሳሰር የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማእከል በጎዛምን እና በአነደድ ወረዳ አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ያለማው የስንዴ ክላስተር ትናንት ተጎብኝቷል። ሚኒስትር ድኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ግብርናውን ከልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ በምርምርና ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ እየተደረገ ይገኛል። ከምርምር ተቋማት የሚወጡ ዝርያዎችን በተሻሻለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ምርት በብዛትና በጥራት ለማቅረብ ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምርም በአካባቢው ከተቋቋመ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ያካሄደው የስንዴ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚቻል ያመላከተ ነው። በምርምር ጣቢያው ላይ እያከናወኑት ያለው የምርምር ስራ እና የመነሻ ዘር ብዜት ለሰብል ልማት ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስትም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የኢትዩጰያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው ምርምር የተሻለውን በመምረጥ ለበለጠ ውጤት የሚያሸጋግር ነው። የደብረ ማርቆስ ምርምር ማእከል አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም በፊት በሄክታር ከ24 እሰከ 25 ኩንታል ይገኝ የነበረውን የስንዴ ምርት ወደ 51 ኩንታል ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን በተደረገ ሙከራ መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡ ማእከሉ ባስተዋወቀው ቴክኖሎጅ ምርታማነትን በእጥፍ በማሳደግ ሀገሪቱ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት በአመት የምታወጣውን ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ በዞኑ ብቻ 90 ሚሊዮን ዶላር ማስቀረት እንደሚቻልም አስረድተዋል። የደብረ ማርቆስ እርሻ ምርምር ማእከል ዳሬክተር አቶ ያለው ማዘንጊያ በበኩላቸው ከኢንስቲትዩቱ የተገኙ “ዋንየ” የዳቦስንዴ፣ ኢቦን” የብቅልገብስና “ቁንጮ”ጤፍ ሰብሎችን በአሲዳማነት የተጠቃ መሬትን በኩታ ገጠም በኖራ በማከም ማልማት ተችሏል። የዳቦ ስንዴው 50 እስከ 70 ኩንታል፣ የብቅል ገብስ 30 እስከ 50 ኩንታል እና ጤፍ ከ25 እስከ 28 ኩንታል በሄክታር ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው። በዚህ ቴክኖሎጂ የማስተዋወቅ የሙከራ ትግበራም 200 ሄክታር መሬት የተሸፈነና ከ380 በላይ አርሶ አደሮች የተሳተፉ መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህ ምርጥ ዘሮች በቀጣይ ዓመት ቴክኖሎጂውን ለሚያስተዋውቁ  ምርጥ ዘር አባዥ አርሶ አደሮች እና ድርጅቶች እንደሚሰራጭ አስረድተዋል። አርሶ አደሮች መካከል የአነደድ ወረዳ የወቢ እነችፎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አእምሮ ላመስግን በበኩላቸው በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከዚህ ቀደም ከ6 ኩንታል የማይበልጥ ምርት ያገኙ እንደነበር ጠቅሰዋል። በዚህ ዓመት በተመሳሳይ መሬት ላይ በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ኖራ በመጠቀም  ካለሙት ስንዴ ከ40 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ጠቅሰዋል። በጉብኝቱ በየደራጀው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና ባለደርሻ አካላት እንዲሁም አርሶ አደሮች ተገኝተዋል። የደብረ ማርቆስ እርሻ ምርምር ማእከል በ43 ሄክታር ማሳ ላይ በሰብል፣ በእጽዋትና በእንስሳት 28 አይነት ምርምሮችን እያከናወነ ይገኛል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም