ቀጥታ፡

በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የችግር መፍቻ አገር በቀል እዉቀቶችን ማጎልበት እንደሚገባ ተገለፀ

ጥቅምት 9/2012 በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሽምግልናና የገዳ ስርዓቶችን ጨምሮ ሌሎች የችግር መፍቻ አገር በቀል እዉቀቶችን ማጎልበት እንደሚገባ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። "የኢትዮጵያ አገር በቀል እዉቀት ለሰላምና ዲሞክራሲ መጎልበት" በሚል መሪ ሃሳብ 5ኛው አገር በቀል የባህልና ኪነ ጥበብ አውደ ጥናት በወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነዉ። ሚኒስትር ድኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ተዋደዉና ተቻችለዉ በፍቅር የሚኖሩባት ሃገር ናት፡፡ ከቅረብ ጊዜ ወዲህ ግን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በክልል፣ በወረዳና በቀበሌ ከፋፍለዉ ህብረተሰቡን ለማተራመስ የሚሰሩ ኃይሎች እየተፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል። ችግሮችን በአገር ውስጥ እውቀት ለመፍታትም ተረትና ምሳሌዎች፣ ቅኔና መንዙማዎች፣ የሽምግልናና ገዳ ስርዓቶች ህብረተሰቡ ላይለያይ ያጋመዱ ጥንታዊ እሴቶቻችን በመሆናቸዉ ትክክለኛ ይዘቱን ከአባቶች በመረዳት ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገር በቀል እዉቀትን የሚያጎለብቱ፣  አንድነትን፣ ፍቅርና መቻቻልን የሚሰብክ ትምህርት በአዲሱ ፎኖተ ካርታ አካቶ እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ሚከሰተዉን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ አዳዲስ አሰራሮች ተዘርግተው ወደ ስራ መግባታቸዉን የገለጹት ፕሮፌሰሩ ይህም ሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናገረዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸዉ ህብረተሰቡ እንደየ እምነቱና እንደየ ብሔሩ ስብጥር ተቻችሎና ተከባብሮ እንዲኖር ያደርግ የነበረው አገር በቀል እውቀት ትኩረት መነፈጉ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚታየው የሰላም መደፍረስ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ትዉልዱ ትክክለኛ ታኩን ተረድቶ አቀር በቀል እዉቀቱን እንዲያጎለብት ዩኒቨርሲቲዉ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር አባተ በተለይ የአፋር፤ የትግሬ፤ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ትስስሮችን የሚያሳዩ ጥናቶችን በመስራት ለአገራዊ አንድነት፤ ሰላምና ዲሞክራሲ መጎልበት የድርሻቸዉን እየተወጡ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶክተር አባተ ገለጻ የወሎን የመቻቻል፤ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌትነትን በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት የልምድ ልዉዉጥ እያደረጉ ነዉ፡፡ በኢትዮጵያ እዛም እዚህም የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለምፈታት መንግስት የሽምግልና፣ የአባገዳና ሌሎች ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶችን ማጎልበት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የግእዝ መምህር ዶክተር ሰርገው ገላው ናቸው፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ተወካይ ዶክተር ደስታ ተስፋዉ በበኩላቸዉ በክልሉ የሚስተዋለዉን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ አገር በቀል እዉቀቶች ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የወሎን ህዝብ የመቻቻል፣ የአንድነትና የመከባበር እሴት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋትም ክልሉ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየዉ አዉደ ጥናት የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቭርሲቲ ሙሁራንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እየተሳተፉ ሲሆን ከ15 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም