በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው " መደመር " መጽሐፍ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ተመረቀ

መቱ/ አምቦ/ፍቼ ኢዜአ ጥቅምት 8/2012 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጻፈው ” መደመር” መጽሐፍ በ ኦሮሚያ በደሌ ፣ መቱ ፣አምቦ እና ፍቼ ከተሞች ዛሬ ተመረቀ። በበደሌው የምረቃ ስነስርዓት የተገኙት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ እንዳሉት  የመደመር ፍልስፍና ልዩነቶችን በማቀራረብና በማቻቻል በዜጎች መሐል ፍቅርና አንድነት እንዲጎለብት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የቡኖ በደሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሻፊ ሁሴን በበኩላቸው ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመደጋገፍና የመቀራረብ እሴት በማጎልበት የተሻለች ሀገር ለመገንባት የመደመር እሳቤ ትልቅ አስተዋጽኦ አንዳለው ገልጸዋል። በተመሳሳይ በመቱ ከተማ የምረቃው ስነስርዓት ሲካሄድ የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ረጋሳ እንደገለጹት የመደመር ፍልስፍና በማህበራዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ያስችላል። መጽሐፉ የመደመርን ፍልስፍና የሚያብራራ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እንዲያነበው ጥሪ አቅርበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአምቦ ከተማ በተከናወነው የምረቃ ስነስርዓት የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አወል አብዲ፣ የኦሮሚያ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እና ሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅና ፍቅር እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አወል አብዲ ገልጸዋል፡፡ መደመር ጠባብነትን፤ ዘረኝነትን፤ አካባባዊነትንና የኃይማኖት አክራሪነትን በማስወገድ ሰው እንደሰውነቱ ብቻ ተከብሮ መኖር አለበት የሚል ሃሳብ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ በምርቃው ስነ- ሰርዓት ዶክተር አብይ ለአንድ አመት ተኩል ያከናወኑትን ተጨባጭ ስራዎችን የሚዳስስ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡ በተመሳሳይ የመጽሐፉ ምረቃ በፍቼ ከተማ በተካሄደበት ወቅት በማንበብ ለሀገር አንድነት ፣ ልማትና እድገት እንደሚጥሩ በስነስርዓቱ ወቅት የተገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በፍቼ ከተማ የሰላሌ ኦሮሞ ባህል ማዕከል በተከናወነው የመጽሐፉ ምረቃ ስነስርዓት ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች ፣ የኦዲፒ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ሌሎች ነዋሪዎች ተሳትፈዋል። የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ታዬ ደንደአ በዚህ ወቅት እንዳሉት መጽሐፉ በሀገሪቱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ልዩነት አቻችለው በአንድነት በመደመር ለመጓዝ አማራጭ የሚያስቀምጥ ነው። በጥልቀት ወደ ፊት በማየት ለሀገሪቱ ሕዝቦች እድገትና ልማት የራሱን አማራጭ የሚያቀርብ ብቻ ሳይሆን ለእርቅ፣ ለሰላምና ለአንድነት በሚጠቅም መልኩ ለአንባብያን የቀረበ በመሆኑ ሁሉም እንዲያነበው መክረዋል። በፍቼ ከተማ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ ሰለሞን ዘውዴ መፅሐፉ ዘለቄታ ያለውና በቀላል ዘዴ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለው በማመን መፅሐፉን ለማንበብ እንደገዙት ገልጸዋል። አቶ መላኩ ሊካሣ በበኩላቸው መፅሐፉ ለፍትህ ፣ እኩልነትና አብሮነት ሰፊ እድል የሚሰጥ ሐሳብ እንዳለው ከተደረጋላቸው ገለጻ መረዳታቸውን ተናግረዋል። አንብበው በጥልቀት ለመገንዘብም መጽሐፉን መግዛታቸው አመልክተዋል። መፅሃፉ በሃገር ደረጃ የሚታየውን መከፋፈልና ልዩነት ወደ አብሮነት በማምጣት ዜጎች ለልማትና እድገት እንዲጥሩ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም