ቀጥታ፡

መደመር" በየኢትዮጵያ ፖለቲካ አማራጭ የሆነ አዲስ የፍልስፍና መስመር ያመላከተ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን

ባህር ዳር/ጎንደር/ወልደያ ጥቅምት 8 / 2012 "መደመር" በሚል ስያሜ ለንባብ የበቃው መጽሐፍ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አማራጭ የሆነ አዲስ የፍልስፍና መስመር ያመላከተ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።

"መደመር" በሚል ስያሜ ለንባብ የበቃው መጽሐፍ  በኢትዮጵያ ፖለቲካ አማራጭ የሆነ አዲስ የፍልስፍና መሥመር ያመላከተ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ መጽሐፍ ዛሬ በባህር ዳር ፣ በጎንደርና ወልድያ ከተሞች ተመርቋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ  ባሀር ዳር ላይ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት እንደተናገሩት መጽሐፉ የኢትዮጵያን የወደፊት የፖለቲካ ፍልስፍና መሥመር ያሳየ ነው።

"የመደመር" ፍልስፍና በጋራ ተባብሮ ለመኖር  ፍላጎት ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንካራ የትስስር ሃሳብ መያዙንም ገልጸዋል።

በተለይም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተባብሮና ተደጋግፎ  በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ ለሚኖረው የአማራ ሕዝብ የመጽሐፉ ስያሜና ይዘት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

"መደመር" የሌሎችን ማንነት አክብሮ ለአገር አንድነት በጋራ መሥራትን እንደሚያመለክትም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

መጽሐፉ የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚያራምዷቸው የመደመር አሳቤዎች ደጋፊ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው በበኩላቸው መጽሐፉ ከጥላቻ ፍቅርን፣  ከተናጠል አብሮነትን፣ ከመገፋፋት መረዳዳትን በአጠቃላይም ትብብርን የሚያጎላና የኢትዮጵያ ሕዝብን ፍላጎት የዳሰሰ ነው ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሞገስ አብርሃ በበኩላቸው መጽሐፉ በኢትዮጵያ መሪነትና  የፖለቲካ ስልጣን በሐሳብ ልዕልና እንደሚመራ እንዳሳየ  ተናግረዋል።

መጽሐፉ አንድነትን ከኅብረ ብሄራዊነት ጋር አጣምሮ መያዙን አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ካለባቸው አገራዊ ኃላፊነት በተጓዳኝ  መጽሐፉን ለንባብ ማብቃታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ በተካሄደው የመጽሐፉ ምረቃ ላይ የተሳተፉ ፖለቲከኞችና ምሁራን የመደመር መጽሐፍ አገራዊው የሚመራበትን ፍኖተ ካርታ የሚያሳይ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

የኢሕአዴግ ጽህፈት ቤት የሕዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተፈራ ደርበው  እንዳሉት መጽሐፉ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ሊያሻግር ይችላል፡፡

መደመር አገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች በመፍታት ዘላቂነት ለማረጋገጥ ይረዳል ያሉት በወልድያ ከተማ በተከናወነው የመጽሐፉ ምረቃ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ናቸው።

መደመር ለሰው ልጅ ክብርና መብት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ የምርታማነትና መዋቅራዊ ችግሮችን የሚፈታ፣ ለወጣቱ ሥራ የሚፈጥርና ሕዝቡን ከፋፍሎ እንደማያይ አስረድተዋል።

ሁሉንም  እኩል የምትጠቅም አገር መገንባትና ብሔራዊ እርቅን ማምጣት፣ የመደመር ፍልስፍና ትኩረቶች መሆናቸው አብራርተዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን በበኩላቸው የአገሪቱን የዘመናት ችግሮች ይፈታል ተብሎ የተዘጋጀውን መጽሐፍ አመራሩና ሕዝቡ እንዲያነበው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም