ቀጥታ፡

የ"መደመር" መፅሐፍ ተመረቀ

አዲስ አበባ፤ ኢዜአ ጥቅምት 8/2012 የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ "መደመር" መፅሐፍ  በሚሊኒየም አዳራሽ ተመረቀ።
መጽሃፉ ከሚያትታቸው አያሌ ቁም ነገሮች መካከል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመደመር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው የሚያመለክተው አንኳር ሀሳብ መሆኑም በምረቃው ላይ የተነበበው የመፅሃፉ ክፍል ያስረዳል።

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተከናወነ ባለው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ ከስምንት ሺህ የሚልቁ ታዳሚያን ተገኝተዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተመለከተው "መደመር" መፅሃፍ ኢትዮጵያ ልትከተላቸው የሚገቡ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ኃብትና የውጭ ግንኙነት አቅጣጫዎችን የሚተነትን ፋኖተ ካርታ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ስልጣን እንደመጡ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና እውን ይሆን ዘንድ አንድነትን ጨምሮ በህዝቦች መካከል የመደመር እሳቤ ወሳኝ መሆኑን ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል ያህል በስፋት ሰብከዋል።

በመፅሃፉ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በአርቲስት አዜብ ወርቁ የተነበበው የመፅሃፉ ክፍል እንደጠቆመው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመደመር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው  የሚያመለክተው ሀሳብ ከመፅሃፉ አንኳር ሀሳቦች መካከል ነው።

"ከመደመር እሴቶች መካከል አንዱ ሃገራዊ አንድነት ነው ፤ሐሃገራዊ አንድነት ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተጋመደ፣ የተሰናሰለና የተዋሃደ መሆኑን አመላካች ነው፤" ሲል ያትታል መፅሃፉ።

መፅሃፉ አክሎም፤ "የኢትዮጵያ ብሔሮች እጣ ፋንታ በጋራ ለማደግ ብቻ  የተሰራ ብቻ እንጂ ተለያይተን ወይም ተነጣጥለን ሉአላዊ ሀገር የነጠላ ሕልውናችንን አስጠብቀን በሰላም መቆየት አንችልም" ሲል ያስገነዝባል።

የኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ አንድነት የምርጫ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ማስጠበቂያ ጉዳይ ጭምርም መሆኑን ያትታል መደመር መፅሃፍ።

ሌላኛው የመደመር እሴት የዜጎች ክብር ነው የሚለው መፅሃፉ የዜጎች ክብር ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ክብራቸው ተጠብቆና ሀገራቸውን መከታ አድርገው እንዲኖሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የመስራት ፍላጎት ነው ሲልም ያትታል። "በስራዎቻችን ሁሉ ዜጎችን አክብሮ ማገልገል በማንኛውም ጉዳይ ላይ በክብር ማማከርና መያዝ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው" ሲልም ይጠቅሳል። መደመር ዘረኝነትንና ጎጠኝነንትን በማስወገድ 'ሰው ሰው' በመሆኑ ብቻ ክብሩና ነፃነቱ እንዲከበር ዘብ መቆም ማለት ነውም ይላል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መፅሃፍ። ብልጽግናን ሌላው የመደመር እሴት መሆኑን የሚተነትነው መፅሃፉ ብልጽግና የዜጎች ስጋዊ የስምና የነፃነት ፍላጎቶች በቀጣይነት ማሟላት እንዲችሉ አቅማቸውን ማሳደግ መሆኑን በማብራራት። በሚሊኒየም አዳራሽ እየተከናወነ ካለው የምረቃ ስነ-ስርዓት በተጨማሪም መጽሐፉ በተመሳሳይ በዛሬው እለት በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ከ30 በላይ ከተሞች ይመረቃል። በአማርኛ፣ እንግሊዝኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎች በአንድ ሚሊዮን ቅጅ ከታተመው መደመር መፅሃፍ የሚገኘው ገቢ ሙሉ ለሙሉ በአገሪቱ ለትምህርት ቤት ግንባታ የሚውል መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም