ቀጥታ፡

የመሰረተ ልማት ግንባታ ብክነትን ለመቀነስ ሰባት ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2012 በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የሚስተዋለውን ብክነት ለመቀነስ ሰባት የተለያዩ ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ የሚያስችል ስምምነት ተደረሰ። የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጄንሲ ሰባት የተለያዩ ተቋማት ለአንድ ዓመት በሚቆይ የጋራ ስምምነት የመግባቢያ ሰነድ አስፈርሟቸዋል። የጋራ ስምምነቱን የፈረሙት ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ናቸው። የተቋማቱ የጋራ ስምምነት ያስፈለገው በአገሪቱ የሚሰሩ መሰረተ ልማትቶች በተቀናጀ መልኩ ባለመሆኑ የገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ብክነትን በማስከተሉ ነው። በተለይም የመንገዶች ባለስልጣን፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ብዙ ጊዜ ያለመቀናጀት ክፍተቱ ጎልቶ ይታያል። ችግሩን ለመፍታት ተቋማቱ በጋራ መስራታቸው አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ተወካይ አቶ ሲሳይ በቀለ በሰጡት አስተያየት የእቅድ ሰነዱ ተቀናጅቶ ለመስራት የሚያስችልና ከብዙ ወጪዎች የሚያድን ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ ይበልጥ በመቀራረብና በመካከርና መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ተወካይ አቶ ሲሳይ ገረመው በበኩላቸው ሁሉም ተቋማት ለአገሪቱ ልማት እስከሰሩ ድረስ ተናበው ማቀድና መፈፀም ይኖርባቸዋል ብለዋል። በቀጣይ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል እቅድና ዲዛይን ማዘጋቀጀትም ያሳፈልጋል ነው ያሉት። የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጄንሲ በ2006 ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም