በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ለመከላከል እየሰራሁ ነው - የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ለመከላከል እየሰራሁ ነው - የግብርና ሚኒስቴር

ጥቅምት 6/2012 የግብርና ሚኒስቴር በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች በተለይ ደግሞ በሶማሌና አፋር ክልልች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ የመከላከል ተግባር በስፋት እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። ክረምቱን ተከትሎ በሚጥለው ከፍተኛ ዝናብ በመታገዝ የሚፈለፈለው የበረሃ አንበጣ በየመን፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ሰሜናዊ ሶማሊያ የምግብ ሰብል ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት እንደሚያደርስ የአለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ) በሐምሌ 2011 ባወጣው ማስጠንቀቂያ ማሳሰቡ ይታወሳል። የበረሃ አንበጣው ከሶማሊያና የመን በመሰደድ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተስፋፋ ሲሆን በተለይ በአፋር፣ አማራ፣ ሶማሊያ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ድሬዳዋ ተሰራጭቷል። አሁን ላይ ያለውን የአየር ጸባይ ተከትሎ የአንበጣ መንጋው ከአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ድሬዳዋ በመመሰደድ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች ላይ መስፈሩን በግብርና ሚኒስቴር የሰብል መከላከል ቡድን መሪ አቶ በላይ ፋንታው ለኢዜአ ተናግረዋል። መንጋው በሰብሎች ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በከፋ ደረጃ በሳር እና በቁጥቋጦ ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ባለሙያው ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ የአንበጣ መንጋው በተጠቀሱት አካባቢዎች እንዳይፈለፈል በአውሮፕላን የታገዘ ከፍተኛ የመከላከል ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ባለሙያው አስታውቀዋል። እስከ አሁን ባለው ሂደት በአፋርና ሶማሌ ክልል በሚገኙ 42 ወረዳዎች 2 ሺህ 693 ሊትር ኬሚካል በመርጨት የመከላከል ስራው በስኬት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የበረሃ አንበጣው ወደ አጎራባች መንደሮች እንዳይስፋፋ የመከላከል ተግባሩ በንቃት በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አቶ በላይ አስታውቀዋል። ከትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የግብርና ቢሮና አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር የበርሃ አንበጣ መንጋውን መስፋፋት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የበረሃ አንበጣውን መስፋፋት በእንጭጩ ለመቅጨት የባለድርሻ አካላት በተለይ ደግሞ የአርሶ አደሮች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያው አሳስበዋል። እንደ ፋኦ መረጃ የአንበጣ መንጋ 174 ስኩዌር ኪሎሜትር በመሸፈን በአንድ ቀን 87 ሺህ ሜትሪክ ቶን አረንጓዴ ተክል ይበላል። በአንድ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ 30 ሚሊዮን የአንበጣ መንጋ እንደሚሰፍርም ተጠቅሷል።