ቀጥታ፡

የሲቪል ማህበረሰብ አዋጁ የአካል ጉዳተኞችን አካታችነት አስገዳጅ ማድረጉ የበለጠ የሚያሰራ ነው ተባለ

ጥቅምት 6/2012 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚል አዲስ የወጣው አዋጅ የአካል ጉዳተኞችን አካታችነት አስገዳጅ ያደረገ በመሆኑ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ገለፀ። የበጎ አድራጎት ማህበራት ድርጅቶችና ማህበራት በሚል ይታወቅ የነበረው የቀድሞው አዋጅ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚል ባለፈው ዓመት ተሻሽሎ መውጣቱ ይታወሳል። አዋጁ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት፣ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ የሲቪክ ማህበራት በሚቀርጿቸው መርሃ ግብሮችና የተለያዩ ተግባራት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የማድረግ ግዴታ ጥሎባቸዋል። ይህ የአካታችነት አስገዳጅ መርህም ባለፈው አዋጅ ከአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት አኳያ የነበሩ ክፍተቶችን የሚቀረፍና የህብረተሰብ ክፍሉንም ጥቅም የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አባይነህ ዋጆ ዛሬ አዋጁን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ያመለከቱት። አዲሱ አደረጃጀት ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ የነበሩ የመብት ጥሰቶችን በመቅረፍ አምራች አካል ጉዳተኞችን ለማፍራት እድል እንደሚፈጥርም አቶ አባይነህ ተናግረዋል። የቀደመው አዋጅ ቁጥር 621∕2000 የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተሰሚነት አፍኖ የያዘ እንደነበር ነው ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ያመለከቱት። "አዲሱ አዋጅ ግን በፓርላማ ቦታ በማግኘት ድምጻችንን እንድናሰማ ከማድረግ ባሻገር አካል ጉዳተኞችን የልማቱ አካል የሚያደርግና የሲቪክ ማህበራቱም አብረውን እንዲሰሩ ምቹ አሰራርን የፈጠረ ነው" ብለዋል። የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ለአንድ አካል ብቻ የማይተው መሆኑን የጠቆሙት አቶ አባይነህ "ለቀጣይ ህይወታችን ብሩህነት ሁሉም የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም በማስከበር፤ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ በባለቤትነት ስሜት ሊሰራበት ይገባል" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የሲቪክ ማህበራትና አጋር አካላት አካታች የሆነ የልማት ተግባር ላይ በማተኮር አምራች አካል ጉዳተኞችን ለመፍጠር እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። በኢትዮጵያ በ2011 ዓም በተደረገው ጥናት 17 ነጥብ 6 ሚሊዮን አካል ጉዳተኖች አሉ። በስብሰባው ላይ እንደተመለከተው ለትምህርት ከደረሱ አካል ጉዳተኞች መካከል የትምህርት እድል እያገኙ ያሉት 8 ነጥብ 6 በመቶ ያህሎቹ ብቻ ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም