የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብር ያስፈልጋል ተባለ
ጥቅምት 6/2012 በኢትዮጵያ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ። ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ መስኮች ያላቸውን ድርሻ ለማጎልበት የቤተሰብና የባህል ተፅዕኖ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዴሞ ፊንላንድ ከተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በሴቶች ተሳትፎ ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና አዘጋጅቷል። በፊንላንድ ካሉ አምስት ፓርቲዎች ውስጥ የአራቱ ሊቀ-መናብርት ሴቶች መሆናቸው ተነግሯል። በአገሪቱ በቅርብ ጊዜ በተካሄደው ምርጫም 40 በመቶ እጩዎች እንዲሁም ከ47 በመቶ በላይ መራጮች ሴቶች እንደነበሩም ተገልጿል። በዚሁ ወቅት የዴሞ ፊንላንድ ሊቀ-መንበርና የፊንላንድ ፓርላማ አባል የሆኑት ሚስ ፔቪ ራሳነን በፊንላንድ የመምረጥና መመረጥ መብትን ያገኙት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1906 ሲሆን በወቅቱም ከ200 የፓርላማ አባላት ውስጥ 19ኙ ሴቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል። በፊንላንድ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንና ይህም አገሪቱ ወደተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ እንድትሸጋገር ማስቻሉን ተናግረዋል። የፆታ እኩልነት ከሰብአዊ ክብር ጋር ተያያዥ ነው ያሉት ሚስ ፔቪ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ ያነሳሉ። በፊንላንድ ሁሉም ልጅ ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት መብት እንዳለው፤ በተለይም ሴቶችን ማስተማር ለቤተሰብና ማህበረሰብ ኑሮ መሻሻል ወሳኝ በመሆኑ ለሴቶች የተለየ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ሴቶችን ለመደገፍ በአገሪቱ ለወለዱ ሴቶች የ10 ወር፣ ለአባቶችም የ54 ቀን ፈቃድ እንደሚሰጥና እንደፍላጎታቸው ደመወዝ እየተከፈላቸው ፈቃዱ መራዘም እንደሚችል ገልፀዋል። የህፃናት ማቆያ በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሩም ዜጎች የቤተሰብና የስራ ህይወታቸውን አመጣጥነው እንዲጓዙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በፊንላንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሴቶች ጉዳይ ላይ ድንበሮችንና ልዩነትን ትተን በትብብር እንሰራለን ያሉት ሚስ ፔቪ ይህም የተሻለ ፖሊሲና ስራዎች እንዲኖሩ አስችሏል ይላሉ። የሴቶችን ተሳትፎ የላቀ ለማድረግ የፓርቲዎችን በጥምረት ተባብሮ መስራት በኢትዮጵያም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። የሴቶችን ተሳታፊነትና ውሳኔ ሰጪነት ለማጎልበት ተባብሮ መስራትን የሚጠይቅ ነውም ብለዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን እንደሚሉት ቅንጅቱ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት ሲሰራ ቆይቷል። በፖለቲካው ዘርፍ እስካሁን በአገሪቱ በተደረጉ ምርጫዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን አቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎች ሲሰጥ ቆይቷል። አሁንም የሴቶችን ተሳትፎ በመጪው ምርጫ ለማሳደግ ፕሮጀክት ቀርፆ በአዲስ አበባና ቤንሻንጉል የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ብቃት የማሳደግና ኀብረተሰቡን የማንቃት ስራዎች ይከወናሉ ብለዋል። በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ይህንኑ ስራ ለመቀጠል መታቀዱን ገልፀዋል። ከ50 በመቶ በላይ ሴቶች ባሉባት አገር ሁሉንም ያካተተ ፖለቲካ ፓርቲ መኖር አስፈላጊ በመሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ማካተት እንዳለባቸውና ሴቶችም መወከል እንዳለባቸው ተናግረዋል። የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል ወይዘሮ ብዙወርቅ ከተተ በበኩላቸው በአገሪቱ ካሉ 139 የተመዘገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድም ሊቀ-መንበር እንደሌለ ገልጸው ቦርዱ የሴት ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን አቅም ለማሳደግ በሁለት ዙር ከ80 በላይ ሴቶች ማሰልጠኑን ተናግረዋል። በረቂቅ የምርጫ ህጉ ላይም ሴቶችን በብዛት ያሳተፈ ፖለቲካ ፓርቲ የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከፍ እንደሚል መካተቱን ተናግረዋል። በምርጫ ታዛቢነትና አስፈፃሚነት ላይም የሴቶች ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት። ቦርዱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማጠናከር የሴቶችን ቁጥር ለማሳደግም ይሰራል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም እንደሚሉት ሴቶችን ወደፊት የሚያመጣ አካል ያለመኖር፣ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎና አሳሪ ባህል በፖለቲካ ውስጥ ቁጥራቸው አነስተኛ እንዲሆን አድርጓል። እናም የፖለቲካ ፓርቲዎች ትናንት ያልነበረውንና በሰፊ የማይታየውን የሴቶችን ቁጥር ለማሳደግ ዛሬ ሊሰሩ ይገባል፤ ባህልም ላይ እንዲሁ ይላሉ። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ የብሄራዊ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ወይዘሪት ካውሰር እድሪስ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር አለመስፋትና በፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት የሚገጥሙ ችግሮች፤ እንዲሁም የማህበረሰቡና ባህል ተፅዕኖ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ገትቶታል ይላሉ። ኢዜማ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ማህበራዊ ፍትህ የሚለውን የፖለቲካ ፍልስፍና ለማሳካት ሴቶችን እንደሚያሳትፍ ተናግረዋል። ከወረዳ ጀምሮ ባለው የኢዜማ አወቃቀር በ366 ወረዳዎች የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ መኖሩንም አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እየጨመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በመንግስት መዋቅር የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሴቶች በሚኒስትርነትና በተለያዩ ከፍተኛ የአመራር ስፍራዎች ላይ ይገኛሉ።