ሀዋሳ ከነማ በአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ ለመሳተፍ ዛሬ ከዩጋንዳው ሲቲ ኦይለርስ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳ ከነማ በአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ ለመሳተፍ ዛሬ ከዩጋንዳው ሲቲ ኦይለርስ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 06/2012 የሀዋሳ ከነማ የቅርጫት ኳስ ክለብ በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ ለመሳተፍ የሚያደርገውን የማጣሪያ ጉዞ ዛሬ ከዩጋንዳው ሲቲ ኦይለርስ ጋር በሚያካሄደው ጨዋታ ይጀምራል። የሀዋሳ ከነማ የቅርጫት ኳስ ክለብ በማጣሪያ ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ዓም ወደ ታንዛንያ ዳሬላም ማቅናቱን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይመር ሃይሌ ለኢዜአ ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ዞን (ፊባ አፍሪካ) እና የአሜሪካ ብሔራዊ የቅርጫት ኳስ ማህበር (ኤን.ቢ.ኤ) በጋራ ያዘጋጀቱ የመጀመሪያው የአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ይካሄዳል። የሊግ ውድድሩ እ.አ.አ ከ1972 ጀምሮ በፊባ አፍሪካ ሲካሄድ የነበረውን የአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ የውድድር ፎርማት በመተካት የሚካሄድ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው የውድድር ፎርማት በየአገራቸው የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ የሆኑ ክለቦች በቀጥታ በቅርጫት ኳስ ሊጉ ላይ ይሳተፉ ነበር። በአዲስ መልክ በሚጀመረው የአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ በባለፈው ዓመት የሊግ ውድድር ውጤታማ የሆኑ ስድስት ክለቦች ያለ ማጣሪያ በቀጥታ ያልፋሉ። በዚሁ መሰረት የአንጎላ፣ ቱኒዚያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሞሮኮና ግብጽ ክለቦች በ2019 የአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ ያለ ማጣሪያ ይሳተፋሉ። ሌሎች ስድስት ክለቦች በማጣሪያ በሊጉ ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ ማለት ነው። 32 ክለቦች በሁለት ዙር ማጣሪያ ከተጫወቱ በኋላ በቀጥታ ካለፉት ስድስት ክለቦች ጋር በመቀላቀል 12 ክለቦች በሊጉ ውድድር ይካፈላሉ። በስድስት ምድብ የተደለደሉት 32ቱ ክለቦች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ማካኔድ ጀምረዋል። በምድብ 4 የማጣሪያ ውድድር የሚሳተፈው የሀዋሳ ከነማ የቅርጫት ኳስ ክለብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከዩጋዳው ሲቲ ኦይለርስ ጋር ያደርጋል። ክለቡ በማጣሪያ ውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆኑ ነው። የአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ በአዲስ መልክ የሚካሄደው ሊጉን ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ ለማሳደግ እንደሆነም የጽህፈት ቤት ሃላፊው አመልክተዋል። እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የማጣሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከነማ ከብሩንዲው ዳይናሞ ቢቢሲ፣ ከሩዋንዳው ፓትሪዮትስ ቢቢሲና ከታንዛንያው ጂኬቲ ክለቦች ጋር ይጫወታል። ከየምድቦቹ አንደኛና ሁለተኛ የወጡት 12 ክለቦች በህዳር ወር 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የሁለተኛው ዙር ማጣሪያ በሁለት ምድብ ተከፍለው በመወዳደር ከአንድ እስከ ሶስት የወጡት ክለቦች በአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ ይሳተፋሉ። በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የአፍሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ የመክፈቻ ጨዋታዎች በአንጎላ፣ ቱኒዚያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሞሮኮና ግብጽ ከተሞች ነው የሚካሄዱት። በሊጉ ውድድር የሚሳተፉት 12 ክለቦች ጨዋታቸውን አድርገው ለፍጻሜ የሚያልፉት ሁለት ክለቦች በሩዋንዳ ኪጋሊ በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም መጨረሻ የፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።