በሰሜናዊ ኬንያ የዳዳብ ስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜናዊ ኬንያ የዳዳብ ስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ ጥቅምት 5 /2012 በሰሜናዊ ኬንያ የዳዳብ ስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያውያን ዜጎች ይሄን የገለጹት ከኬንያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ተወካዮች እንዲሁም በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ አለም ዳዳብ ውስጥ ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። ዜጎቹ ወደ አገራቸው በመመለስ እንደሌሎች ወገኖቻቸው ህይወታቸውን መምራት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። እስከ 30 ዓመት ለሚሆን ጊዜ በስደተኛ ካምፕ ውስጥ የቆዩት 4 ሺህ 500 ያህል ስደተኞች መንግስትና የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያረግላቸው ጠይቀዋል። የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ምክትል ኃላፊ ዎልፑርጋ ኢንግፕሬክት በበኩላቸው ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ አለም በበኩላቸው በተመሳሳይ መንግስትም ዜጎቹን ወደ አገራቸው ለማስገባት የሚቻለውን እንደሚያደርግ በመግለጽ ከስደተኞቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠታቸውም ነው በመግለጫው የተጠቆመው። ከዓለማችን ትልቁ የስደተኞች ካምፕ የሆነው ዳዳብ በአሁኑ ወቅት 200 ሺህ ያህል ስደተኞች እንደሚገኙና ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሶማሊያ ስደተኞች መሆናቸውም ተጠቅሷል። አብዛኛዎቹ በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መካከል አብዛኞቹ ከኦሮሚያ፣ ሱማሌ እና ጋምቤላ ክልሎች የመጡ መሆናቸው ኤምባሲው የላከው መግለጫ ያሳያል። በሌላ በኩል በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው ስትራትሞር ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱን ኤምባሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የስትራትሞር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተር ማርቆስ ሚገሪ ትናንት ናይሮቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት ከአምባሳደር መለስ ዓለም ጋር ውይይት አድርገዋል። ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት እንደሚፈልግና ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የነጻ ትምህርት ዕድል ለመስጠት ፍቃደኛ መሆኑንም ገልጸዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ፍላጎት አድንቀው ኤምባሲው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ማርቆስ ሚገሪ በቀጣይ ከኤምባሲው ጋር አብሮ መስራት የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት አምባሳደሩ ዩኒቨርሲቲውን እንዲጎበኙና ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን እንዲያገኙ ግብዣ አቅርበዋል። ስትራትሞር ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ 1961 እንደተመሰረተና በተለይም ደግሞ በሂሳብ አያያዝና በህግ አለምአቀፍ እውቅና ያለው ዩኒቨርስቲ እንደሆነም የኤምባሲው መግለጫ ያትታል።