ቀጥታ፡

በማህበረሰቡና በአካባቢ ላይ ጉዳት በሚያደርሱ የማዕድን አምራቾች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ

አዲስ አበባ ጥቅምት 5 /2012   በማህበረሰቡና አካባቢ ላይ ጉዳት በሚያደርሱ ማዕድን አምራቾች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የማዕድንና የጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ። ዓለም አቀፍ የማዕድን ግልጽነት ኢኒሼቲቭ ቦርድ ስብሳባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ቦርዱ በማዕድንና በነዳጅ ዘርፍ ላይ ያለውን አጠቃላይ አስተዳደር የሚቆጣጠር ሲሆን በዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበርክት የሚያግዝ ነው። በዚሁ ወቅት የማዕድንና ጋዝ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርካቶ እንደገለጹት ሁሉም የማዕድን ስራ አካባቢንና ማህበረሰብን ከግምት ያስገባ መሆን አለበት። ከዚህ አልፎ ጉዳት በሚያደርሱት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ፤ ነገር ግን በቅድሚያ ከኩባንያዎቹ ጋር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። በኩባንያዎቹ ላይ ተከታታይ ግምገማ በማካሄድ በአካባቢና በሰው ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና ሌሎች ሁኔታዎችም ይዳሰሳሉ ብለዋል። ከዓለም አቀፍ የማዕድን ግልጽነት ኢኒሼቲቭ ቦርድ ጋር በመሆን በተለያዩ ድርጅቶች ላይ ግምገማ መካሄዱንም ጠቁመዋል። ኩባንያዎቹም ግኝቱን መሰረት በማድረግ በተቀመጠው ደረጃ መሰረት እንዲያስተካክሉ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። እንዲያስተካክሉ የተነገራቸው ኩባንያዎች አሰራራቸውን ካላሻሻሉ በቀጣይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል። የዓለም አቀፍ የማዕድን ግልጽነት ኢኒሼቲቭ ቦርድ የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ መርጋ ቀነዓ ቦርዱ በማዕድንና በነዳጅ ዘርፍ ያለውን አጠቃላይ አስተዳደር ከመቆጣጠር በተጨማሪ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበርክት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የጾታ አካታችነትና የአካባቢ ጥበቃ ተጽዕኖን መገምገምና የማዕድን አመራረቱ በተቀመጠው ደረጃ መሰረት መፈጸሙን የማረጋግጥ ተግባራት ያከናውናል ነው ያሉት። ከዚህ በተጨማሪ ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ከመንግስት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል። በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች፣ መንግስትና ሲቪል ማህበራት በዘርፉ የግልጽነት እና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲጎለብት በጋራ መስራት አለባቸውም ሲሉም ጠቁመዋል። የመንግስት አሰራርን በማጠናከርና የፈቃድ አሰጣጡን በተቀመጠው ህግ መሰረት በእውቀት በመምራት ውጤት ለማምጣት እየሰራን ነው ብለዋል። ደካማና ጠንካራ ጎኖችን በመለየት ጥናቶች በመስራት፣ በማዕድን ማምረቻ አካባቢ ለሚኖሩ ማህበረሰቦች በተለያዩ ዘዴዎች ግንዛቤ መፍጠርና ከመንግስትና ከኩባንያዎች ጋር በውጤቱ ላይ በመወያየት ያሉትን ችግሮች መፍታት ይገባልም ነው ያሉት። ኩባንያዎቹ አቅማቸውን በመገንባትና በቂ እውቀት በመያዝ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ መስራት አለባቸው ብለዋል። ከዚህ በፊት በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት ለማስተካከል ከጥር 2010 ዓ.ም ቀደም ሲል የነበረውን ችግር የሚያሻሽል ህግ መውጣቱን አስታውሰዋል። በዘርፉ የተሰማሩ 16 ኩባንያዎች በ2010 ዓም ለማህበረሰብ ልማት በርካታ ገንዘብ ማፍሰሳቸው በጥናት መረጋገጡንም አስታውቀዋል ። እስከ 300 ሚሊዮን ብር ለማህበራዊ አገልግሎት በማዋል መንገድ፣ ውሃ፣ ትምህርት ቤት እና ድልድይ የሰሩ ኩባንያዎችም እንዳሉም ጠቅሰዋል። ነገር ግን የተሰራው ልማት ህብረተሰቡ የሚፈልገው ሳይሆን ራሳቸው የሚፈልጉት በመሆኑ የባለቤትነት ስሜት ለማሳደግ አልተቻለም፤ ይህንንም በቀጣይ ማስተካከል ይገባል ብለዋል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም