የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ
ጥቅምት 5/2012 በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ የረር ተራራ አካባቢ ሰራተኛውን በማስተባበር የተከላቸውን ችግኞች እንክብካቤ አድርጓል። በእንክብካቤ መርሃ ግብሩ ላይ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የደን ልማት ባለሙያዎችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል። ባለፈው ክረምት በአገር አቀፍ ደረጃ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉ የሚታወስ ሲሆን ኮሚሽኑም በአድአ ወረዳ የፈረንጅ ጽድ፣ የሀበሻ ጽድና ወይራን ጨምሮ ከአምስት ሺህ በላይ ችግኞችን ተክሎ ነበር። የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ዘመቻውን በመቀላቀልም አረም ማረም፣ ሳር ማጨድና ለችግኞች እድገት መሰናክል የሆኑ ነገሮችን የማንሳት ተግባራት ተከናውነዋል። በኮሚሽኑ የደን ልማት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ቢተው ሺባባው እንደገለጹት፤ ችግኝ መትከል በራሱ ግብ ባለመሆኑ ተንከባክቦ ለሚፈለገው ዓላማ ማደረስ ተገቢ ነው። ኮሚሽኑ ችግኞችን መንከባከብ ቁልፍ ስራው አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል። በተለይ ክልሎች የችግኝ እንክብካቤ ማድረግ የሚችሉበት መመሪያ መላኩን የተናገሩት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ ከተከላ በኋላ ምን ምን ተግባራት መተግበር እንደሚኖርባቸው ስልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል። ስለአረም አወጋገድ፣ ውኃ ማጠጣትና መኮትኮት የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ አቶ ቢተው ገለጻ፤ የደን ጥበቃና እንክብካቤ እየተካሄደና በቀጣይ ችግኝ የሚተከልባቸውን አዳዲስ ቦታዎች የመለየት ተግባር እየተከናወነ ነው። በሁለተኛው የእድገትና ትራንፎርሜሽ እቅድ መሰረት በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በችግኝ ለመሸፈን ግብ መጣሉን ያስታወሱት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ ''በዚህ ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ተተክሏል'' ብለዋል። የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው ኮሚሽኑ አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ኮሚቴ አባልና የቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ በመሆን አረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴውን ሲመራ እንደነበር አስታውሰዋል። በኢትዮጵያ ችግኞች ቢተከሉም በቂ እንክብካቤ የማይደረግ በመሆኑ የመጽደቅ ምጣኔው አነስተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤው ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል። ኮሚሽኑም ችግኝ የተከለባቸው ቦታዎችን ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ማድረግ፣ ማረምና ውኃ ማጠጣት ስራዎች እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመው፤ ሌሎች ተቋማት ችግኞችን ውኃ የማጠጣትና መንከባከብ ተግባርን እንዳይዘነጉ መልዕክት አስተላልፈዋል። ፕሮፌሰር ፍቃዱ እንደሚሉት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉ ችግኞችን በተመለከተ ድጋፍ የሚያደርግ የቴክኒክ ቡድን ወደ ተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ተልከዋል። በእንክብካቤ መርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ይሁን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ''የሚተከሉ ችግኞች አብዛኞቹ እንዲጸድቁ ሁሉም ዜጋ የመንከባከብ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት'' ብለዋል። ''ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ እስከ ተከላው ድረስ ያለውም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል'' ብለዋል። ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት መሰረት የአገሪቷ የደን ሽፋን 15 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።