ቀጥታ፡

የዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ ጥቅምት 5 /2012  የዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቶ ስራውን በይፋ ጀምሯል። የድርጅቱ የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን ሐምሌ 2010 ዓ.ም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተፈረመው ስምምነት መሰረት ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ስራውን በይፋ ጀምሯል። በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት የአህጉሪቱ የሜቲዎሮሎጂ ጽህፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የአፍሪካ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ የሚያበረክቱት አስተዋዕኦ ከፍ እንዲል ያደርገዋል። የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው የድርጅቱ የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት ከጄኔቫ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ስለተደረገው ጥረት አውስተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትና የበርካታ አገራት ዲፕሎማቶች መቀመጫ በመሆኗ ለጽህፈት ቤቱ መቀመጫነት ታጭተው ከነበሩ ስምንት የአፍሪካ አገራት መካከል መመረጧን ገልጸዋል። እንደ ዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ፕሮፌሰር ፒተሪ ታላስ ገለጻ ጽህፈት ቤቱ ወደ ኢትዮጵያ መዛወሩ አህጉሪቷን ከድርጅቱ በቅርበት ተጠቃሚ ለማድረግ ይረዳል። የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ለማጠናከርና ለማሻሻል፣ የአየር ሁኔታና ጠባይ አስተዳደርን ለማቀናጀት እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የጎላ ሚና አለው ብለዋል። የጽህፈት ቤቱ ወደ አዲስ አበባ መዛወር በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የአየር ሁኔታ ጠባይ መረጃና ፍላጎት ለማርካትና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላልም ነው የተባለው። እየዘመነ ከመጣው የትራንስፖርትና የግንባታ ዘርፍ አኳያ የግብርና ምርትና የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን ለመጨመር፣ በአየር ሁኔታና መረጃ ላይ ይበልጥ ለመተማመንም እንዲሁ። የዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት በተባበሩት መንግሥታት ስር ሆኖ በአየር ሁኔታና ጠባይ ላይ የሚሰራ ተቋም ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም