ዋልያዎቹ ነገ ወደ ሩዋንዳ ያቀናሉ - ኢዜአ አማርኛ
ዋልያዎቹ ነገ ወደ ሩዋንዳ ያቀናሉ
አዲስ አበባ ጥቅምት 5 /2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና /ቻን/ ውድድር ላለበት የማጣሪያ ጨዋታ ነገ ወደ ሩዋንዳ ያቀናል። የአፍሪካ አገራት ቡድኖች በካሜሮን አዘጋጅነት በ2020 ለሚካሄደው የቻን ውድድር የማጣሪያ ጨዋታ እያካሄዱ ነው። ዋልያዎቹም ነገ ወደ ስፍራው አቅንተው ጨዋታቸውን ከነገ በስቲያ ዓርብ ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው በመቀሌ ስታዲየም ከሩዋንዳ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 1 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል። በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ዋልያዎቹ ለመልሱ ጨዋታ 20 ተጫዋቾች የተካተቱ ሲሆን ያሬድ ባዬ በጉዳት ምክንያት በቡድኑ አልተካተተም ተብሏል። አሰልጣኙ በእሱ ምትክ አንተነህ ተስፋዬን መተካታቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት በቡድኑ ውስጥ ተጫዋቾችና አሰልጣኞችን ጨምሮ 29 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ወደ ስፋራው እንደሚያቀና ገልጸዋል። ዋልያዎቹ በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ የጅቡቲ አቻቸውን 5 ለ 3 በማሸነፍ ነው ለመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ከሩዋንዳ ጋር የተደለደሉት። ባለፈው ዓመት ዋልያዎቹ በመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸው በሩዋንዳ ተሸንፈው ነበር ከቻን ውድድር ውጭ የሆኑት።