ቀጥታ፡

በሩብ ዓመቱ ከቡናና ቅመማ ቅመም ምርት ከ234 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ኢዜአ፣ጥቅምት 5/2012 ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡናና ቅመማ ቅመም ምርት ከ234 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳህለማሪያም ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሶስት ወራት ከ82 ሺህ 211 ቶን በላይ  የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 234.59 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር በመጠን 20,302.49 ቶን በገቢ ደግሞ 26.17 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለውም ነው ያስረዱት፡፡

ምርቱ ከተላከባቸው ሀገሮች መካከል ጀርመን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ እንደሚገኙበትም ጠቅሰዋል፡፡

ግዢ ከፈጸሙ ሀገራት መካከል ጀርመን 46.80 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ቀዳሚ ስትሆን ፣ ሳውዲ አረቢያ 33.45 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ግዢ በመፈፀም ሁለተኛ፣ ጃፓን ደግሞ 26.48 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ግዢ በመፈጸም  ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሆነች ተናግረዋል፡፡

በ2012 በጀት ዓመት ሦስት ወራት የተላከዉ ቡና ሲዳማ ከ26 ሺህ ቶን በላይ፣ ነቀምት ከ20 ሺህ ቶን በላይ እና ጅማ ከ15 ሺህ ቶን በላይ በማስመዝገብ ደረጃ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የዓለም የቡና ዋጋ ብዙም መሻሻል ያልታየበት ቢሆንም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተለያዩ ስራዎችን እየተከናወነ መሆኑን ነው አቶ ሳህለማሪያም የጠቆሙት፡፡

ከሚከናወኑት ተግባራት መካከልም ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው  ዓለማቀፍ  የቡና ቅምሳሻ ውድድር፣ ሁለተኛው ዓለማቀፍ የቡና ፌስቲቫል ኤግዚቢሽንና የንግድ ትርኢት የሀገራችንን የቡና ምርት በዓለም አቀፍ መድረኮች በማስተዋወቅ ገቢው እንዲጨምር በማድረግ  አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።

በ2012 በጀት ዓመት በድምሩ 341 ሺህ 192 ነጥብ 89 ቶን ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ወደ ውጭ በመላክ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም