ቀጥታ፡

ኃላፊነትን የሚረከብ ትውልድ ለመፍጠር መንፈሳዊ ተቋማት መጠንከር አለባቸው

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ኃላፊነትን የሚረከብ ትውልድ ለመፍጠር መንፈሳዊ ተቋማት ጠንካራ ስራ መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ። የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ዛሬ ሁለገብ የመጽሐፍ ቅዱስና የፎቶ ኤግዚቢሽን  አካሂዷል። ማህበሩ ያስገነባው አዲስ ህንጻም ተመርቋል። የማህበሩ  ዋና ፀሃፊ አቶ ይልማ ጌታሁን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ "ኃላፊነትን የሚረከብ ትውልድ ለመፍጠር መንፈሳዊ ተቋማት ብዙ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል"። አዲሱን ትውልድ በጥሩ ስነ ምግባር አንፆ ለማሳደግና የተሻለ አገር ተረካቢና ኃላፊነትን በብቃት የሚወጣ  ትውልድ ለመፍጠር  ተከታታይነት ያለው የሃይማኖት ተቋማት የአስተምህሮ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል። ማህበሩ ቀደም ብሎ የጀመራቸውን ስራዎችን በማጠናከርና ለህዝቡ ሁለገብ አገልግሎትን ለመስጠት የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጣይ በትኩረት  እንደሚሰራ ተናግረዋል። የተሻለ ትውልድ ቀርጾ ለአገርና ለወገን  እንዲበጁ በማድረግ  በኩልም መንፈሳዊ ተቋማት፣ የተለያዩ  ባለድርሻ  አካላትና መንግስት በርካታ ስራዎችን ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ተስፋጽዮን ደለለው በበኩላቸው፤ "ትውልዱ ንባብን ባህል ለማድረግ ኃላፊነትን መውስድ  አለበት" ብለዋል ። አሁን ከቀድሞ የተሻለ  መጻሕፍትና የማንበቢያ ስፍራዎች በተለይም ንባብን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ያሉ በመሆኑ የተሻለ ለማድረግ  መሰራት አለበት ነው ያሉት ። ኢግዚቢሽኑ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2012ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም