ቀጥታ፡

ሽልማቱ የጋምቤላ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ለውጡን ለማራመድ የሚያደርገውን ጥረት ያጠናክረዋል- ር/መ ኡሞድ

ጋምቤላ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ የተሰጠው ሽልማት የጋምቤላ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ለውጡን ለማራመድ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያጠናክረው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። ''ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ያገኙት የኖቤል ሽልማት የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር ሥራቸው ድምር ውጤት ነው'' በማለት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በሰልፉ ላይ እንደተናገሩት የክልሉ ሕዝብና መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አመራር የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ይጥራሉ። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበረከተላቸው ሽልማት ለኢትዮጵውያን ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካ ጭምር ኩራት መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም በአገሪቱ የተጀመረውን የአንድነትና የመደመር እሳቤ ዳር ለማድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት በአገር ውስጥና በጉረቤት አገሮች ባከናወኗቸው የሰላም ፣ የአንድነትና የዴሞክራሲ ሥራዎች መሆኑንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በኢትዮ- ኤርትራ መካከል የነበረውን የሰላም ችግር ያለማንም አደራዳሪነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈታ ያደረጉ መሪ መሆናቸውን አስታውሰዋል። እንዲሁም በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በኬንያና በሌሎች ጉረቤት አገሮች ሰላምና  መረጋጋት ለማስፈን ያከናወኗቸው ተግባራት ለሽልማት እንዳበቋቸው ገልጸዋል። በድጋፍ ሰልፉ ከተካፈሉት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ደፍር ተሬሳ በሰጡት አስተያየት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ሽልማት ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵውያን ጭምር ነው ብለዋል። በመሆኑም የተገኘው ድል ለአገሪቱ ብሎም ለአካባቢው ሰላምና አንድነት እውን እንዲሆን ለሁሉም ዜጎች የተሰጠ የቤት ሥራ መሆኑን ተናግረዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በተሰጣቸው ዓለም አቀፍ ሽልማት መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ አቶ ገዛኸኝ ከበደ ናቸው። በመሆኑም ዜጎች ከጎናቸው በመሆን የሰላም ግንባታውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት ኡሞድ አኝዋሃ በሰጠው አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ሽልማት በአገር ውስጥና በውጭ ሲሰቃዩ የነበሩ የኢትዮጵያ ዜጎች በማስፈታትና ሰላም እንዲሰፍን በማደረጋቸው ጭምር ነው። ስለሆነም በእርሳቸው የተጀመረው ዕራይ ግቡን እንዲመታ የጋምቤላ ወጣቶች ድጋፋቸውን ያጠናክራሉ ብሏል። በጋምቤላ ከተማ አራቱም አቅጣጫ በመነሳት መድርሻውን የጋምቤላ ስታዲዬም ባደረገው ሰልፍ ላይ ፣የከተማው ነዋሪዎች፣የመንግሥት ሠራተኞና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም