በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታ መቐለ ከተማ መከላከያን 1ለ0 አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታ መቐለ ከተማ መከላከያን 1ለ0 አሸነፈ
አዲስ አበባ ሰኔ10/2010 በ2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በተካሄደ ጨዋታ መቐለ ከተማ መከላከያን 1ለ0 አሸንፏል። በመቐለ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አማኑኤል ገብረሚካኤል ባስቆጠራት ግብ መቐለ ከተማ አሸናፊ የሆነ ሲሆን ያገኘው ሶስት ነጥብ ዋንጫውን ለማንሳት በሚደረገው ፉክክር እንዲቆይ አድርጎታል። በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም በተደረገ ሌላ የሊጉ ጨዋታ አዳማ ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል። ለአዳማ ከተማ ቡልቻ ሹራ ለአርባምንጭ ከተማ እንዳለ ከበደ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ፋሲል ከተማ ሲዳማ ቡናን 2ለ1፣ ጅማ አባጅፋር ወልዲያ ከተማን 2ለ0 እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን 3ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል። ድሬዳዋ ከተማና ኢትዮ ኤሌትሪክ ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል። በሃዋሳና በወላይታ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሊያደርጉት የነበረው የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የሶስት ሳምንት መርሃ ግብሮች በቀረቡት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን ለማንሳት የሚደረገው ፉክክር አጓጊ ሆኗል። የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 48 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ መቐለ ከተማ በ46 ነጥብ ሶስተኛ ሆኖ ይከተላል። ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ አርባ ምንጭ ከተማና ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ኦኪኪ አፎላቢ በ17 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።