በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተፃፈው "መደመር" መፅሃፍ በመጪው ቅዳሜ ይመረቃል - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተፃፈው "መደመር" መፅሃፍ በመጪው ቅዳሜ ይመረቃል
ጥቅምት 4/2012 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው "መደመር" መፅሃፍ በመጪው ቅዳሜ በታላቅ ስነ-ስርዓት ይመረቃል። ከመጽሃፉ የሚገኘው ገቢ ሙሉ ለሙሉ በአገሪቱ ለትምህርት ቤት ግንባታ የሚውል መሆኑን ታውቋል። ዶክተር አብይ ወደስልጣን እንደመጡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድና በመላው አፍሪካ ጭምር ዘላቂ ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና እውን ይሆን ዘንድ በህዝቦች መካከል የመደመር እሳቤ ወሳኝ መሆኑን ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል ያህል በስፋት ሰብከዋል። በመደመር አስተሳሰብና ፋይዳዎቹ ላይ የሚያጠነጥነው መፅሃፉ በመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ በሚገኙ 20 ከተሞች በይፋ የሚመረቅ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል። በምረቃ መድረኩ የመፅሃፉን ይዘት የተመለከተ አጭር ፅሁፍም ይቀርባል ነው የተባለው። የመደመር እሳቤው የአገሪቷን ቁልፍ ችግሮች እንዴት እንደሚፈታና ወደ ህብረተሰቡ በቀላሉ እንዴት እንደሚደርስ በስነ-ስርዓቱ ላይ በዝርዝር የሚገለጽ መሆኑንም አቶ ንጉሱ አብራርተዋል። ከአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ከሚከናወነው የምረቃ ስነ-ስርዓት በተጨማሪ መፅሃፉ በአዳማ፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ጋምቤላ፣ ጅግጅጋ፣ አሰላ፣ ሀረርና ሰመራን ጨምሮ በ20 ከተሞችም የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ታዋቂ ሰዎች የአገር ሽማግሌዎች ምሁራንና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበትይመረቃል ተብሏል። መፅሃፉን ለመመረቅ በክልል ከተሞች የሚከናወነው ስነ-ስርዓት የየክልሎቹን ባህላዊ እሴቶች በሚያንፀባርቁ ሁነቶች የሚታጀብ ይሆናል። መጽሃፉ በአንድ ሚሊዮን ቅጅ በአማርኛና እንግሊዘኛ፣ ኦሮምኛና በሌሎች ቋንቋዎች በኢትዮጵያና አሜሪካ መታተሙም ታውቋል። መፅሃፉ ከሁለት ሳምንታት በኋላም በአሜሪካ ዋሽንግተን፣ ሎስአንጀለስና ሚኒሶታ እንደዚሁም በኬንያ ናይሮቢ በታላቅ ስነ-ስርዓት ይመረቃል። የመጽሃፉ ሽያጭ 300 ብር ሲሆን ከሽያጩ የሚገኘው ገቢም በመላ የአገሪቱ ክፍሎች ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት እንደሚውል ታውቋል።