በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የግለሰቦች ግጭት የህይወትና የንብረት ጉዳት አስከተለ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የግለሰቦች ግጭት የህይወትና የንብረት ጉዳት አስከተለ
ጥቅምት 4/2012 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በግለሰቦች መካከል ትላንት ማታ የተነሳ ግጭት በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር ጌትነት አልታሰብ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ግጭቱ ወደ ቡድን በማምራቱ የህይወትና የአካል ጉዳት ከማስከተሉም ባለፈ ለበርካታ ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል። በዞኑ ጎንደር ዙሪያ ወረዳ አምቦበር፣ ማጫና ቡርቧክስ እንዲሁም በጎንደር ከተማ ስር ባሉ ጠዳ፣ ምንዝሮ፣ ፈንጠርና አየር ጤና በተባሉ ቀበሌዎች ግጭቱ ተስፋፍቶ የህይወትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ማስከተሉን ገልጸዋል። "አሁን በክልሉ ልዩ ኃይል፣ የአካባቢው ህዝብ፣ ፖሊስና ሚሊሻ አባላት ባደረጉት የማረጋጋት ስራ ሁከት የለም" ያሉት ኮማንደሩ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በጥፋቱ ላይ እጃቸው አለ የተባሉ አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። ግጭቱን ለማስቆም የአካባቢው ማህበረሰብ ያደረገውን የማረጋጋት ስራ አድንቀው አለመግባባቶችን በግልግል እና በህግ ከመፍታት ይልቅ ወደ ሌሎች ማስፋፋት አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው አጠቃላይ የጉዳቱ መጠን ተጣርቶ ለህዝብ እንደሚገለጽ ተናግረዋል።