ቀጥታ፡

ክልሉ አገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ከብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ጋር በትብብር ይሰራል--የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

ሀዋሳ ኢዜአ ጥቅምት 03/2012 ክልላዊና አገራዊ ሠላምን ለማረጋገጥ ከብሐራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ጋር በትብብር እንደሚሰሩ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፁ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ የጋራ የዕርቀ ሠላም ሥራዎችን በተመለከተ ከኮሚሽኑ አባላት ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል ፡፡ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በዚህ ወቅት እንደተናገሩት አስተዳደራቸው ለሠላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ። የዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ ከክልሉ በጋራ ለመስራት አቅዶ መንቀሳቀሱ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸውም አስረድተዋል ፡፡ ወቅቱ ያለፉ ቁርሾዎችንና መገፋፋቶችን አስወግደን ኢትዮጵያን የመከባበር ፣ የፍቅርና ሁሉም ዜጎቿ በዕኩልነትና በነፃነት የሚኖሩባት ሀገር አድርገን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የምንሰራበት ትክክለኛው ጊዜ ነው ብለዋል ፡፡ ይህንን ሀሳብ የጠነሰሱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አለም አቀፍ የሠላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውም ኢትዮጵያ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን በራሷ ልጆች  ሠላምን ማምጣት የምትችል ሀገር መሆኗን ለዓለም ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡ የኮሚሽኑ አባላት በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑን ያወሱት አቶ ርስቱ ምንም እንኳን የሠላም ባለቤት ራሱ ህዝቡ ቢሆንም የሐይማኖትና የባህል መሪዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች የሚያደርጉት ጥረት አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል ። ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ በቂ የሆነ ሀብት የተቸራትና ምቹ የአየር ንብረት ባለቤት ብትሆንም ይህንን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላችን ለድህነትና ለግጭት ምሳሌ የምንሆንበት ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት አቶ ርስቱ ሁሉም ባለበት ቆም ብሎ ሊያጤነው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል ፡፡ የዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ የጀመረው ዘላቂ ሠላምን የማረጋገጥ ሥራ ዕጅግ ከባድ ቢሆንም ይሳካል የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸውም ገልፀዋል ፡፡ የኮሚሽኑ ወደ ክልሉ መምጣት ትልቅ እድል እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንንም በታላቅ አክብሮት እንደሚቀበሉትና ክልላዊና ሀገራዊ ሠላም ለማረጋገጥ በመተባበር እንደሚሠሩ ነው የገለፁት ፡፡ ደቡብ ክልል የብዝሀነት ባለፀጋ ፤ አስተማሪ የሆኑ በርካታ የሠላም እሴቶች ያሉበት እንደሆነ ገልፀው ነገር ግን የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኑ አልፎ አልፎ ከጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት የተነሳ ህዝቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ኩነቶች እንደሚፈጠሩ አስረድተዋል ፡፡ ትውልዱ ያሉትን እሴቶች ተጠቅሞ ዘላቂ ሠላምን ማስፈን እንዲችልም ኮሚሽኑ ከሀይማኖትና ከባህል አባቶች ጋር ተቀራርቦ የሚሰራበትን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል ፡፡ በተመሳሳይም ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር ቅርበት በመፍጠር ሰፊ ሥራዎች እንደሚሠረሩ ገልፀዋል ፡፡ የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ሰብሳቢ የኢትዮዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው ኢትዮጵያ በህዝቦቿ መካከል ለዘመናት በተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች የተነሳ የተደራረቡ ቁርሾዎች ታክመው ሰላሟ ተጠብቆ በብልፅግና እንድትቀጥል ለማድረግ ዕርቀ ሠላም ማውረድ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ ይህ ሂደት ሕጋዊ መሰረት እንዲኖረውም የዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ ሊቋቋም መቻሉን አስረድተዋል ፡፡ ዕርቀ ሠላሙ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተከባብረውና ተጋግዘው እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ በነፃነት ተንቀሳቅሰው በጋራ መበልፀግ እንዲችሉ የተመቻቸ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል ፡፡ ይህን ሥራ የተሳካ ለማድረግም ከክልሎች ጋር ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ፡፡ ለዚህም የሚረዳ መልካም የሥራ ግንኙነት ለመፍጠር ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር መምከሩ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ነው ያስረዱት ፡፡ የኮሚሽኑ አባል ከሆኑት መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበባት መምህር አቶ አያልነህ ሙላቱ በበኩላቸው ሠላምና ዕርቅ በህዝቡ ዘንድ ያለ እሴት መሆኑን ገልፀው ወደ ህዝቡ ለመውረድና ወደ ተግባር እንዲተረጎም ለማገዝ ከአስተዳደር አካላት ጋር በጋራ መስራት ማስፈለጉን አስረድተዋል ፡፡ ይህንን ጥረት ከዳር ለማድረስ ጥበብ ከፍተኛ ሚና አላት ያሉት አቶ አያልነህ በዚህ ረገድ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል ፡፡ በህዝቡ ዘንድ ለዓመታት የተጠራቀሙ ቁርሾዎች መንስኤዎቻቸው ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን የተናገሩት ሌላው አባል ዶክተር አበራ ደሬሳ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ችግሮችን ከምንጫቸው በመፍታት ዘላቂ ሠላምን ለማምጣት እንደሚሠራ ገልፀዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም