በኢትዮጵያ የጸሀይ ኃይል ማመንጫ ለማስገንባት አክዋ ተብሎ ከሚጠራው ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የጸሀይ ኃይል ማመንጫ ለማስገንባት አክዋ ተብሎ ከሚጠራው ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈረመ
ጥቅምት 4/2012 ኢትዮጵያ የጸሀይ ኃይል ማመንጫ ለማስገንባት አክዋ ተብሎ ከሚጠራው የሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያ ጋር የ300 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ፈረመች። ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የኩባንያው ፕሬዚደንት ፓዲ ፓድማናታን(Paddy Padmanathan) ናቸው። ኩባንያው የጸሀይ ሀይል ማመንጫዎችን የሚገነባው 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ነው። በአፋር ክልል ዲቸቶ(Dicheto) እንዲሁም በሶማሌ ክልል ደግሞ ጋደ (gad) ተብለው የሚጠሩ ፕሮጀክቶች ናቸው የሚገነቡት። ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዳቸው 125 በአጠቃላይ 250 ሜጋ ዋት የጸሀይ ኃይል እንደሚያመነጩም ነው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በስምምነቱ ወቅት የተናገሩት። ይህም በአገሪቷ ያለውን የኃይል አቅርቦት ክፍተት የሚሞላና የታዳሽ ኃይልን በማሳደግ አገሪቷ የተያዘችውን የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴንም መደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው ብለዋል። እንዲሁም ሁለቱ አገሮች ያላቸውን ግንኙነት የሚያጠናክርና የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሀብቶች በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎችም እንዲሳተፉ የሚያበረታታ ነውም ብለዋል። ኩባንያው የሚያመነጨውን የጸሀይ ኃይል ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ለአገሪቷ ያቀርባልም ብለዋል። ሌሎች ዝርዝር ስምምነቶች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እንደሚከናወንም አስረድተዋል። ኩባንያው በዘርፉ ካለው የካበተ ልምድና አቅም ተጠቅሞ ውጤታማ እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የኩባንያው ፕሬዚደንት ፓዲ ፓድማናተን በበኩላቸው ፕሮጀክቱን በኢትዮጵያ ለመገንባት እድል በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውንና መንግስት ላደረገው ድጋፍም ምስጋና እንዳላቸው ተናግረዋል። ይህ ስምምነትም በሳዑዲ ዓረቢያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት የሚያጠናክርና የሚያሻሽል እንደሆነም ተናግረዋል። በውሃና በጸሀይ የሚሰሩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት ለአገሪቷ ያለውን የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ፓዲ ስምምነቱም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው ብለዋል። የጸሀይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅና ውጤታማ ለማድረግ ኩባንያው አቅሙና ቁርጠኝነት እንዳለውም ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል።