የሩሲያ ፕሬዚዳንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የ'እንኳን ደስ አለዎት' መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የ'እንኳን ደስ አለዎት' መልዕክት አስተላለፉ

ኢዜአ ጥቅምት 4/2012 የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የ'እንኳን ደስ አለዎት' መልዕክት አስተላለፉ። ፕሬዚዳንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቴሌግራም ባስተላለፉት መልዕክት የኖቤል ኮሚቴው ውሳኔ ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደሰላም ለመመለስ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማቱ ተገቢ እንደሆነም አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣናው ሰላም ለማረጋገጥና የአፍሪካ አህጉር ዓለማቀፋዊ ትስስር እንዲጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ የራሺያ መንግስት ከጎናቸው የሚቆም መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን በመልዕክታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤናና ስኬት ተመኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገሮች መካከል ሰላምንና አብሮነት ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን የማይደፈረውን ደፍረው ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ተፈርጀው ለእስር የተዳረጉትን አቶ ዳንኤል በቀለን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አድርገው የሾሟቸው ሲሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር አድርገዋቸዋል። በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት በአገሪቱ መፃኢ እድል ላይ ውይይት ማድረጋቸው ሌላው ስኬታቸው ነው። በውጭ አገር ተቀምጠው የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር ሲጥሩ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋርም ሰላም በማውረድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ሜዳውን ከፍተውላቸዋል። የደህንነቱንና የፍትህ ዘርፉንም ተአማኒ ለማድረግ በሩን ክፍት በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጡ እያገዙ ነው። በአገሪቱ ወደ ኋላ የቀረውን የሴቶች ተሳትፎ ከነበረበት አዘቅት በማውጣት ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸውም አድርገዋል።