ቀጥታ፡

የሰንደቅ ዓላማ ክብር በመጠበቅ አገራዊ ለውጥ ማራመድ እንደሚገባ የሁለት ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድር አሳሰቡ

ጋምቤላ/ጅግጅጋ ጥቅምት 3 /2012 የማንነት መገለጫ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ ክብር በመጠበቅ አገራዊ ለውጥ ማራመድ እንደሚገባ የጋምቤላና የሶማሌ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድር አስገነዘቡ። ''ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሃነታችን ድምር ውጤት የአንድነታችን ምሰሶ ነው!''በሚል መሪ ቃል 12ኛው ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በጋምቤላና በጅግጅጋ ከተሞች ተከብሯል። የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት የኢትየጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አንድነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ሊጠበቅ ይገባዋል። አገራዊ ለውጡን ለማራመድ ጠንከሮ መስራት ያስፈልጋል። ''ሰንደቅ ዓላማችን ብዙ ሆነን አንድ ያደረገን የማንነትና የሉዓላዊት መገለጫ ዓርማችን ነው'' ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ስለ ሰንደቅ ዓላማ ያውን ፍቅር በማሳደግ በየደረጃው ያሉት ምክር ቤቶች የጀመሯውን ሥራዎች እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል። የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ በዓል የኢፊዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓበይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በሆኑበት ማግስት መከበሩ የተለየ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል። የክልሉ ምክር ቤት አፈ- ጉባዔ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው ምክር ቤቱ በተለይም ወጣቱ ትውልድለሰንደቅ ዓላማ ያለውን ፍቅርና ክብር ለማሳደግ በትምህርት ቤቶች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በዘንድሮው ዓመት በዓሉ በትምህርት ቤቶችና በመንግሥታዊ ተቋማት ከመስከረም 30/2012 ጀምሮ መከበሩን አስታውቀዋል። የጋምቤላ ከተማ ነዋሪው ወጣት ኡኩኝ ኡቦንግ በሰጠው አስተያየት በግንዛቤ እጥረት ለሰንደቅ ዓላማ የሚሰጠው ክብርና አጠቃቀም ክፍተት እንደሚታይበት ተናግሯል። በመሆንም ለኅብረተሰቡ በሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል ብሏል። ሰንደቅ ዓላማው የኢትዮጵያ ብሄር/ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአንድነት መገለጫ ዓርማ በመሆኑ ለሕዝቡ በቂ ግንዛቤ መስጠት ይገባል ያለው ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ አባል ሳጅን ወንዴ አሰፋ ናቸው። በተመሳሳይ በጅግጅጋ በተከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ላይ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐሙድ  'ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነት ዓርማችን ነው'' ብለዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በ12ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ላይ እንደተናገሩት የክልሉ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማውን ማክበርና ማስከበር ይገባዋል። በሰንደቅ ዓላማው ሥር በመሰባሰብ ከሌሎች ኢትዮጵውያን ጋር ለጋራ ዕድገት እንዲተጋም አሳስበዋል።የክልል ምክር ቤቱ አፈ ጉባ' አቶ አብዲ መሐመድ ሰንደቅ ዓላማውን የሚፃረሩ ተግባራት በጋራ መታገል ያስፈልጋል ብለዋል። በበዓሉ ላይ ፌዴራልና የክልሉ ሰንዴቅ ዓላማዎች አሰቃቀል ሥነ ሥርዓት በሁለቱ ባለሥልጣናት ተከናውኗል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም