ቀጥታ፡

አገራዊ ለውጡን ለማጠናከር እተጋለሁ-- ኢዜማ

ደሴ ጥቅምት 3 / 2012 "እየታገልን ያለነው በአገራችን ሕዝቦች ላይ ሲፈጸም የነበረውን ግፍ ዳግም ለመድገም ሳይሆን፤ የተገኘው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው" ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ፓርቲ አስታወቀ። ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮችና በድርጅቱ አቋሞች ዙሪያ ከኮምቦልቻና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር በኮምቦልቻ ከተማ ተወያይቷል፡፡ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩትፓርቲው  እየታገለ ያለው በሕዝቡ ትግልና ግንባር ቀደም ተዋናይነት የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ነው፡፡ ሕዝቡም አንድነቱን ጠብቆ የአካባቢውን ሰላም በማስከበርና የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ለውጡን በመቀልበስ የሚጥሩ ኃይሎችን ነቅቶ መጠበቅ አለበት ብለዋል። ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ የፖለቲካ ጥቅመኞችንና ሴረኞችን ለመከላከልና አስተሳሰባቸውን ለማምከንም በመርህ ላይ ተመስርቶ የሚታገል ጠንካራ መሪና ሕዝብ እንደሚያስፈልግ  ምክትል ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ ፓርቲው ለሕዝብ ጥቅም፣ ለአገር አንድነትና ሰላም ይሰራል ያሉት ዶክተር ጫኔ፤  ልዩነትን የሚፈጥሩፖሊሲዎችና መመሪያዎች እንዲስተካከሉ ከመንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በአገሪቱ ከ400 በላይ ወረዳዎች ላይ ጽህፈት ቤቶቹን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ  መሆኑን  አስረድተዋል። የኮምቦልቻ ከተማ ኢዜማ ጽህፈት ቤት ሊቀመንበር አቶ ታሪኩ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ለአገር አንድነት፤ ሰላምና ዲሞክራሲ መጎልበት በመስራት ለለውጡ ቀጣይነት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ አንድ በሚያደርጉት ላይ በማተኮር በአባቶቹ ዳር ድንበሯን ጠብቀው ያቆየሉትን አገር የባህልና የታሪክ እሴቶች በማስቀጠልም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሱልጣን መሐመድ እንደገለጹት ትውልዱ ያጠፋውን በመምከር፣ በፍቅርና በይቅርታ አልፎ የአባቶችን ታሪክ መድገም ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ሌላው ተሳታፊ አቶ ያህያ ሺፈራው የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ሁሉን አሳታፊ ሕገ መንግሥት እንዲፀድቅ፣ሥራ ፈጠራ እንዲጎለብትና ኢኮኖሚው እንዲያድግ  ጥረቱን ማጠናከር እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ በውይይቱ የኮምቦልቻ ከተማና አካባቢዋነዋሪዎች፤ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም