'አጋር' መባላችን በራስ መተማመናችንን በመቀነስ የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳንወጣ አድርጓል - ርዕሰ መስተዳድሮቹ - ኢዜአ አማርኛ
'አጋር' መባላችን በራስ መተማመናችንን በመቀነስ የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳንወጣ አድርጓል - ርዕሰ መስተዳድሮቹ
አዲስ አበባ ጥቅምት 3 /2012 'አጋር' መባላችን በራስ መተማመናችንን በመቀነስ የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳንወጣ አድርጓል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ገለጹ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከሁለት አስርት በላይ ለሆነ ጊዜ በአራት አባል ፓርቲዎችና በአምስት አጋር ፓርቲዎች መንግስት ሆኖ እየመራ ይገኛል። ኢህአዴግ "ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) " በተባሉ አራት እህት ድርጅቶች የተፈጠረ ግንባር ነው። ግንባሩ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ቤጉህዴፓ)፣ የሐረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን)፣ የሶማሌ ህዝቦች ዴሞራሲያዊ ፓርቲ (ሶህዴፓ) እና የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) የተባሉ አምስት ፓርቲዎችን ደግሞ በአጋርነት ይዟል። 'አጋር' ፓርቲዎቹ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ውስን በመሆኑ በየጊዜው ቅሬታ ሲነሳ እንደነበረ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሁለት ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ገልጸዋል። በአንድ አገር ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ክልሎችን በእኩል ደረጃ በውሳኔ ሰጪነት ማሳተፍ አንዱ የዴሞክራሲ ስርዓት ማሳያ እንደሆነም የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድሮች አስረድተዋል። የኢህአዴግ አጋር ደርጅቶች በአገሪቱ በሚወጡ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ላይ እኩል ተሳትፎ እንዳልነበራቸውም ገልጸዋል። በተለይ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ''የኢህአዴግ አጋር ተብለን ከግንባሩ ጋር እንድንሰራ መደረጉ የራስ መተማመንን የሚቀንስና የተጣለብንን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንዳንወጣ አድርጎናል'' ብለዋል። የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ነናየቤንሻልጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውህደት ከተቀየረ በኋላ በታዳጊ ክልሎች የሚመረጡ አመራሮችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በራስ መተማንንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት መወጣት እንደሚያስችላቸውም ርዕሰ መስተዳድሮቹ ገልጸዋል። ወደፊት ይመሰረታል ተብሎ ለሚታሰበው የግንባሩ ውህደት ክልሎቹ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ኢህአዴግ ከአገራዊ ለውጡ በፊት የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የሶማሌ ክልሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል። በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የአጋር ፓርቲዎቹን ጥያቄ ለመመለስ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህደት ለመለወጥ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔው አቅጣጫ አስቀምጧል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ከሸገር ኤፍ ኤም 102 ነጥብ 1 ከቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢህአዴግ አሁን ባለው ቁመና እንደማይቀጥል አረጋግጠዋል።