ቀጥታ፡

ለጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰጠው ሽልማት ለሰላምና ለልማት የበለጠ ተነሳሽነት የሚፈጥር ነው - ምሁራን

መቱ /ሰመራ /ነቀምቴ ጥቅምት 3 /2012  ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘታቸው በሀገር ውስጥና በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ አስተማማኝ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑን የመቱ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናገሩ::

ምሁራኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው ከኢትዮጵያውያን ባለፈ መላው አፍሪካውያንን ያስደሰተና ያኮራ ነው::

በዩኒቨርስቲው የጤና ሳይንስ ፋከልቲ መምህር አቶ ፀጋዬ በርኬሳ እንዳሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገር ውስጥና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ለሰላም መስፈን የሰሩት ስራ በቀጠናው አዲስ የትብብርና መደጋገፍ መንፈስ እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው::

ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ዜጎች ከውጭ ወደ አገራቸው አንዲገቡና የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት አገሪቱን ከተጋረጠባት ፈተና ማላቀቃቸው ለወደፊት ትልቅ ተስፋን ያሳደረ እንደሆነ ተናግረዋል::

የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችና አስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ተካልኝ ቀጄላ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘታቸው የአፍሪካ ቀንድ አገራት ለኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ይበልጥ እንዲሰሩ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል::

አገራቱ በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መስኮች በማስተሳሰር የሚያደርጉትን ጥረት በፖለቲካና ኢኮኖሚ ጠንካራና  ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው::

" በተለይ ብዙ የሰው ህይወት የቀጠፈውና ላለፉት 20 አመታት አስቸጋሪ ሆኖ የቆየውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ያለመግባባትና ግጭት በአጭር ጊዜ የፈቱበት አካሄድ ራሱን የቻለ መፅሐፍ የሚወጣው ነው" ብለዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘታቸው ይዘው የተነሱት የመደመር ፍልስፍና ውጤት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋሩማ አብዲሳ ናቸው::

ከሁለት አመታት በፊት ከፍተኛ ስጋት ተደቅኖባት የነበረችው አገር ተረክበው ህዝቡን አንድ ለማድረግ ያከናወኑዋቸው ተግባራትና ያስመዘገቡት ውጤት በአጭር ጊዜ ይሆናል ተብሎ ያልተገመተ እንደሆነም ገልፀዋል::

ከአገር ውስጥ አልፎም ቅራኔ ውስጥ የነበሩ የአፍሪካ ቀንድ አገራትም በመካከላቸው አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ የጀመሩት በዚሁ የመደመር ፍልስፍና እንደሆነ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸውም በአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል የተጀመረውን አዲስ የትስስርና የወዳጅነት ጅምር የሚያጠናክር እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶክተር አብይ አህመድ ያሸነፉት የሰላም ኖቤል ሽልማት ለሀገራዊ የፖለቲካ ሽግግር ትልቅ አቅም እንደሚሆን በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፀዋል ።

የአፋር ህዝብ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሃመድ ዳዉድ እንደተናገሩት ለዶክተር አብይ የተሰጠው የሰላም ኖቤል ሽልማቱ ችሮታ ሳይሆን በጥረትና ትጋት የተገኘ የጠንካራ ስራ ውጤት ነው ብለዋል ።

የአፋር አብዮታዊና ዴሞክራሲዊ አንድነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ መሃመድ አወል ወግሪስ በበኩላቸው የዶክተር አብይ ሽልማት ከሀገር ውስጥ የሪፎርም ስራዎች ጎን ለጎን በግጭት ለሚታመሰው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሰላም አየር እንዲነፍስ ለሰሩት በጎ ስራ የተሰጠ ትክክለኛ ሽልማት ነው ሲሉ ገልፀውታል ።

የአፋር ነጻ አዉጪ ግንባር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሀንፈሬ መሃመድ በበኩላቸው የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ኩራቱና ክብሩ ለጠቅላይ ሚነስቴሩ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እውነተኛ ኢትዮጵያዊያን ጭምር ነው  ብለዋል ።

በተያያዘ ዜና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት የሀገሪቱ ዜጎች የመደመር ፍልስፍናን በማጠናከር ወደ ላቀ እድገትና ብልፅግና እንድንሸጋገር መነሳሳት የሚፈጥር ነው ሲሉ የነቀምቴ ከተማና የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገልፀዋል ።

ነዋሪዎቹ የኖቤል ሽልማቱን በመደገፍ ባዳረጉት ደማቅ የድጋፍ ሰልፍ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም ለሰላምና ለአገራዊ አንድነት በፅናት እንደሚቆሙ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም