የጅቡቲ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ጉዳት አድርሷል የሚባለው ወሬ ሐሰት ነው- የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጅቡቲ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ጉዳት አድርሷል የሚባለው ወሬ ሐሰት ነው- የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 3/2012 "የጅቡቲ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ወደ አፋር ክልል በመግባት ጉዳት አደረሰ በሚል የሚሰራጨው ወሬ ሐሰት ነው" ሲል የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር ገለፀ። "የጅቡቲ ጦር የኢትዮጵያን ድንብር ተሻግሮ በአፋር በኩል ዜጎች ላይ ጉዳት አደረሰ" የሚለው ወሬ ሐሰት መሆኑን በመከላከያ ሚኒስቴር የምክትል ኤታማዥር ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ ተናግረዋል። በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲዎችና አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን "በአፋር ድንበር በኩል የጅቡቲ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ጉዳት አደረሰ" በሚል የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑ ተገልጿል። ጅቡቲም ኢትዮጵያን የመውረር ሐሳብ እንደማታራምድና የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጥብቅ መሆኑን ተናግረዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ለግጭት የሚዳርግ ምንም አይነት ተጨባጭ ምክንያት አለመኖሩን የገለጹት ኮሎኔል ተስፋዬ እየተሰራጨ ያለው መረጃም ትክክል አለመሆኑንም አብራርተዋል። ይሁን እንጂ በአካባቢው አልፎ አልፎ በግጦሽ፣ ውሃና በሌሎች ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶች መኖራቸውን አስታውሰው፤ በክልሉ በዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የመከላከያ ሰራዊት በስፍራው ተገኝቶ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።