የኖቤል የሠላም ሽልማት ድል ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ላይም ሊደገም ይገባል ተባለ

44
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 2 / 2012 የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሠላም ሽልማት ድል ሁሉም የእርሳቸውን አርዓያ በመከተል አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ የሚደረገውን ጥረትም ለመድገም ሊረባረብ ይገባል ተባለ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሠላም ሽልማት ማግኘታቸውን ምክንያት በማድረግ በዛሬው እለት በአሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የደስታ መግለጫ ሰልፎች ተካሂደዋል። ከነዚህ ከተሞች መካከል አንዱ የሰበታ ከተማ አስተዳደር ሲሆን በሰልፉ በርካታ ሰዎች ተገኝተዋል። የከተማው ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘት ከኦሮሞና ከኢትዮጵያ ህዝብ ባለፈ ለመላው አፍሪካ ህዝብ ኩራት ነው። ይህ የሽልማት ድልም ሁሉም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በእውቀት፣ በትዕግስት፣ በጥበብና በፍቅር ማከናወን እንደሚገባ ያስተማረ ተግባር ነው ብለዋል። አገሪቱን ካለችበት ድህነት ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት አርዓያ የሚሆንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈር በመከተል ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ለማስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ነፃነት እንዲሰፍን በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን  በትዕግስት፣ በማስተዋል፣ በእውቀትና በፍቅር በመምራታቸው ለውጤታማነት መብቃታቸውን ገልጸው፤ ''ለዚህም የኖቤል የሰላም ሽልማት ይገባቸዋል'' ብለዋል። በዚህም ተግባራቸው በማህበረሰቡ ከፍተኛ ድጋፍና እውቅና እየሰጣቸው መሆኑንና ለስኬታማነታቸውም ከጎናቸው ለመቆም በፍቃደኝነት ለድጋፍ  መውጣታቸውን ገልጸዋል። ሰልፈኞቹ  “የኖቤል የሠላም ሽልማት የመደመር ፍልስፍና ውጤትና አሸናፊ ሃሳብ ዓለም ዓቀፍ ሽልማትን ያመጣል” የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ወጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  ከትናንት በስቲያ  የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ  መሆናቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም