አዲሱ የማሽላ ዝርያ ምርታቸውን እንዳሳደገላቸው የቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

72
ጥቅምት 2 ቀን 2012 በምርምር የተገኘውን "መልካም" የተባለ አዲስ የማሽላ ዝርያን በኩታ ገጠም ተጠቅመው ማልማታቸው ምርታማነታቸው እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉን በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ። በወረዳው በኩታ ገጠም የተዘራው አዲሱ የማሽላ ሰብል ከክልልና ከወረዳ በተውጣጡ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጎብኝተዋል። አርሶ አደር ያሲን መሃመድ በቃሉ ወረዳ የ016 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በምርምር የተገኘው "መልካም" የተባለ አዲስ የማሽላ ዝርያ መጠቀማቸው ምርታቸው ማሳደግ እንዳስቻላቸው በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት በፊት በሩብ ሄክታር መሬት ላይ ማሽላ ዘርተው ከአራት ኩንታል በታች ያገኙ የነበረው  በአዲሱ ዝርያ በመተካት ምርታቸው ከእጥፍ በላይ ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል። ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ይማም ሙሄ በበኩላቸው “ አዲሱ ማሽላ ዝርያ ምርታችን ከማሳደጉም በላይ በኩታ ገጠም መዝራታችን ተባይን በመከላከል፣ በአረምና በኩትኳቶ ያወጡትን የነበረው ጉልበትና ወጪ እንዲቀንስ ያስቻለ ነው “ብለዋል። ባለፈው የመኸር ወቅት በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ያለሙት ማሽላ በቃያው በጥሩ ሁኔታ ላይ በመሆኑ ከ18 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ አመልክተዋል። እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ የበፊቱ ማሽላ ለመድረስ እስከ ሰባት ወር ከመቆየቱ ባለፈ በንፋስ እንደሚወቅድ፣ በአገዳ ቆርቁርና ትል የሚጠቃ ነው፤ በቂ ምርት አይሰጥም ነበር። አዲሱ ዝርያ ግን በሶስት ወራት ውስጥ የሚደርስና ችግርን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት መስጠት እንደሚችል በተግባር ማረጋገጥ ችለዋል። የአካባቢው የግብርና ባለሙያ አቶ አክሊሉ አበራ እንዳሉት በ2010/2011 የምርት ወቅት በሁለት አርሶ አደር ማሳ ላይ የተደረገውን ሙከራ ውጤት በማስገኘቱ ባለፈው መኸር 35 አርሶ አደሮች የማሽላ ዝርያውን ተጠቅመው ዘጠኝ ሄታር መሬት እንዲያለሙ ተደርጓል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በበኩላቸው በምርምር የተገኙ አዳዲስ የማሽላ ዝርያዎችን ለማስፋት ከክልልና ምስራቅ አማራ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በጉብኝቱ በማሳተፍ ውጤቱን እንዲያዩ ማድረጋቸው ገልዋል። መልካም፣ ጊራና አንድ እና ኤሰ ኤች አንድ የተባሉ የማሽላ ዝርያዎች በሽታን በመቋቋምና ፈጥነው የሚደርሱ በመሆናቸው የዝናብና እርጥበት አጠር ለሆኑ ምስራቅ አማራ አካባቢዎች ምቹ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ የዝርያዎቹ ውጤት ለአርሶ አደሩ በተግባርና በልምድ ልውውጥ በማሳየት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ነው። የአርሶ አደሩ የማምረት ፍላጎት እየጨመረ ነው። በምርምር የተገኙት ማሽላ ዝርያዎች ከ20 ኩንታል በታች የነበረውን የነባሩን ዝርያ ምርት በእጥፍ ማሳደግ እንደተቻለ መረጋገጡም ተመልክቷል። በመኸሩ ወቅት በዞኑ ከ230 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ከ60 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማሽላ ማልማታቸውንና ከዚህመከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ተብሏል፡፡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሰፋ “የተሻሻሉ የማሽላ ዝርያዎችን በሁሉም የክልሉ ዞኖች በማስተዋወቅ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ በትኩረት እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡ በተለይ ምስራቅ አማራ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እርጥበት አጠር ቦታዎች ላይ ፈጥነው የሚደርሱና በሽታን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በጥናት ተለይተው ወደ ስራ መግባታቸው አመልክተዋል። በአማራ ክልል በማሽላ ከለማው ከ700 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማሳ ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም