የስፖርት ቱሪዝም ማስፋፋትን ዓላማ ያደረገው የወንጪ ሐይቅ የተራራ ላይ ሩጫ ተካሄደ

50
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 2/2012 የስፖርት ቱሪዝም ማስፋፋትን ዓላማ ያደረገው የወንጪ ሐይቅ የተራራ ላይ ሩጫ ለስድስተኛ ጊዜ ትናንት ተካሄዷል። ከአዲስ አበባ 155 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ዙሪያ የተካሄደው የተራራ ላይ ሩጫ 21 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ሲሆን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተከናውኗል። በውድድሩ የጣልያን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሊባኖስ፣ ሩሲያ፣ ስፔን፣ ፓርቹጋል፣ አንጎላ፣ጋናና ናይጄሪያን ጨምሮ 20 ከውጭ አገሮች የተውጣጡ 250 የውጭ አገር ዜጎችም ተሳትፈዋል። የውድድሩ አዘጋጅ የሪያ ኢትዮጵያ ስፖርት የውድድር ዳይሬክተር አቶ ቃለአብ ጌታነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የውድድሩ አላማ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋትና የቱሪዝም መስህቦችን ማስተዋወቅ ነው። የወንጪ ሐይቅ ዙሪያ ያሉትን የተፈጥሮ መስህቦች የአካባቢውን ነዋሪ ቦታውን በማስጎብኘት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ያልተለመደውን የተራራ ላይ ሩጫ እንዲያድግና እንዲስፋፋ ማድረግም ሌላኛው የውድድሩ አላማ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በቀጣይ የማራቶን ውድድር ማከናወን፣ ውድድሩን በዓመት ሁለት ጊዜ ማካሄድና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ የማድረግ ስራ እንደሚከናወንም ነው አቶ ቃለአብ ያስረዱት። በ21 ኪሎ ሜትር ወንዶች ሳምሶን በቀለ፣ እንግሊዛዊው ቻርሊ ዴቪስ እና ፈረንሳዊው ማቲያስ ሲሞን ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ፤ በሴቶች እንግሊዛዊቷ በርኒ ስሚዝ፣ ኢልሳ ቫን ሚርሎ ከኔዘርላንድ እና ስዊዘርላንዳዊቷ አና ቡር ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ እንዲወዳደሩ በተደረገበት የወንጪ ሐይቅ ዙሪያና አካባቢው ነዋሪዎች 21 ኪሎ ሜትር የተራራ ላይ ሩጫ አሰፋ ጉርሞ፣ ቶሌራ ደግነትና አያንሳ ደግነት ከአንድ እስከ ሶስት ወጥተዋል። በተጨማሪም በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወንድ ዴንማርካዊው አንድሪያስ ባውማን፣ ጆሐንስ ቶርማን ከስዊድን እና ማቲያስ ሊማ ከጣልያን በሴቶች ኤደን ነጋሽ፣ ማርሊን ጆሐንሰን ከፈረንሳይ እና ኢቫና ጋርሲያ ከኢኳዶር ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። በ21 ኪሎ ሜትር የወንጪ ሐይቅ ዙሪያና አካባቢው ነዋሪዎች የተራራ ላይ ሩጫ ለተሳተፉት ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት በሌሎች ውድድሮች ለተሳተፉት የውጭ ዜጎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማልያ፣ ቡናና ሌሎች የባህል ስጦታዎች ተበርክቷላቸዋል። የሪያ ኢትዮጵያ ስፖርት፣ የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን የስፖርት ጽህፈት ቤትና የቱሪዝም ኢትዮጵያ የስራ ኃላፊዎች ለተወዳዳሪዎች የተዘጋጀውን የማበረታቻ ሽልማት አበርክተዋል። ወንጪ ሐይቅ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በወንጪ ወረዳ ከአዲስ አበባ 155 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ እጅግ በጣም ያማረ ተፈጥሯዊ መስህብ ያለው ስፍራ ነው። ወንጪ ሐይቅ በ3 ሺህ 380 ሜትር ከፍታ ባለ ተራራ ላይ ሐይቅ፣ ፍልውኃና ደን፣ ብርቅዬ አዕዋፋትን፣ በደሴቱም ጥንታዊውን የቅዱስ ቂርቆስ ገዳም የያዘ ትልቅ መስህብ ያለው ቦታ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም