የቀብሪ ደሃር -ዋርዴር አስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

90
ጅግጅጋ ኢዜአ ጥቅምት 2 / 2012 በሶማሌ ክልል የቀብሪ ደሃር -ዋርዴር አስፋልት መንገድ ግንባታ በ1ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ ተጀመረ ። በቀብሪ ደሃር ከተማ የመንገዱ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር  ትናንት ተካሂዷል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ከመንግሥት በተመደበ በጀት የሚካሄደው ግንባታ በሁለቱ ከተሞች መካከል የሚደረገውን ጉዞ በአንድ ሰዓት ያህል ያሳጥረዋል። በዚህም ሁለት ሰዓት ተኩል የሚወስደውን ጉዞ ወደ አንድ ሰዓት ከ30 ደቂቃ ያደርገዋል፡፡ 139 ኪሎ ሜትር የሆነው መንገድ ከጠጠር ወደ አስፋልት ደረጃ እንደሚያድግም  አስታውቀዋል። ግንባታውንም ማክሮ የተሰኘ አገር በቀል የሥራ ተቋራጭ እንደሚያከናውነው ተናግረዋል። የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐሙድ በበኩላቸው መንገዱ በዚህ ዓመት በክልሉ በአስፋልት ደረጃ ከሚሰሩ ሰባት መንገዶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። መንገዶቹ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል ቢሆኑም፤  በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው  ሳይጀመሩ መቆየታቸውን አመልከተዋል። መንገዱ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጠቀሜታው የላቀ ነው ብለዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ የአገር ሽማግሌዎችና  የአካባቢው ኅብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም