ችግሮችን በመነጋገርና በመደማመጥ በመፍታት ሰላምን ማስፈን ይገባል- በሀዋሳ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮችን በመነጋገርና በመደማመጥ በመፍታት ሰላምን ማስፈን ይገባል- በሀዋሳ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች
ጥቅምት 1 / 2012 ችግሮችን በመነጋገር ለመፍታት ዝግጁ የሆነ ትውልድ በመፍጠር የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚገባ በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተስተዋለ ያለው ጉልበትና ሀይልን በመጠቀም ፍላጎትን ለማሟላት የሚደረግ እንቅስቃሴ የሀገሪቱን ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል። በዚህ መንገድ ተጉዘው ለጊዜው ቢሳካላቸውም በህግ ተጠያቂ ከመሆን ሊድኑ እንደማይችሉ ተናግረዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አያሌው ምትኩ እንዳሉት በሀገሪቱ በመነጋገር፣ በመደማመጥና በመመካከር ልዩነትን የምንፈታባቸው እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መጥተዋል። “እኔ ያልኩት ብቻ ይደመጥ የሚል አባዜ እየተጠናወተን ነው'' ያሉት አቶ አያሌው ከገጠር ይልቅ በከተሞች በሀይልና በጉልበት የማመን ዝንባሌ ጎልቶ እየታየ መሆኑ ተናግረዋል ። "ሰላማችንን የሚያደፈርሱ ሀይሎችን በይሉኝታም ይሁን በጥቅም ዝም ብለን አናልፋቸውም" ብለዋል ። "የሀይማኖትና በጎሳ ግጭት አየገነነ የመጋጨት ሰው መሆንና ኢትዮጵያዊነት ዋጋ አልባ ሲሆን እየተስተዋለ ነው" ሲሉም ተናግረዋል ። በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ጉሰኝነትን የሚሰብኩና ብሄር የሚያቀነቅኑ ግለሰቦች እየተበራከቱ ቢመጡም የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነቱን መርጦ ዝም በማለቱ አፍራሾች እሳቱን እንደፈለጉ ማቀጣጠል ሳይችሉ መቅረታቸውን ተናግረዋል ። ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ በተለይም መምህራን በትምህርት ቤት የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ህዝቡን ስለ ሰላምና አንድነት ማስተማርና መምከር እንዳለባቸው አመላክተዋል ። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የደኢህዴን ሴቶች ሊግ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነይማ ሙኒር በበኩላቸው በሀይል የመጠቀም አባዜ ዋንኛ ተጎጂ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። ግጭት በቤተሰብ ውስጥም ሳይቀር የሚፈጠር መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለመፍታት እየተሸረሸረ የመጣውን የመነጋገርና የመመካከር ልምድ ለማጎልበት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። ለመከባበር ወሳኙ መደማመጥ በመሆኑ በተለይም ወጣቶች ምክንያታዊ ለሆኑ ፍላጎታቸው ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ በውይይት የማመን ልምዳቸው እንዲጎለብት መላው ህብረተሰብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ቻላቸው ማሞ ወላጆች ለልጆቻው ተገቢውን የስነ ምግባር ትምህርት በመስጠት መቻቻል፣ መከባበርና አብሮነት እንዲጎለብት ማድረግ ይችላሉ። የመቻቻል፤ ታላቅ ታናሹን የማክበር፤ ወጣቶች የወላጆቻቸውን፣ የሽማግሌዎችንና የሀይማኖት አባቶችን ምክር መስማት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። "መልካም እሴቶቻችን በአንዳንድ ቦታ ላይ ሲጣሱ ይታያሉ" ያሉት አቶ ቻላቸው ሽማግሌዎች የሚሉትን ያለመስማት፣ ያለማዳመጥና ያለማክበር ባህል እየተቀየረ በመምጣቱ አሁን እየተፈጠረ ላለው ግጭት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል ። የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታየ ጨጋ አሁን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ቀጣይነት አንዲኖረው የሰላሙ ባለቤት የሆነው ህዝቡ በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል። " በሀይልና በጉልበት የሚያምኑ አካላትን በመምከር ለመመለስ መስራት አለበት" ጠቁመዋል። "የሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም ነው" ያሉት ኃላፊው እድገትና ዲሞክራሲውም እርስ በእርስ የሚመጋገቡ ሰላም ላይ የሚሰሩ ስራዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስገንዘበዋል ። እንደ ኃላፊው ገለጻ ህዝቡ ለሰላምና ለህግ የበላይነት መከበር ህዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በአጋርነት ሊሰራ ይገባል፡፡ አራተኛ ተናጋሪ አቶ ታየ ጨጋ 03: 29 መግቢያ"የሚሰጠው..........አለኝ" መውጫ 04:09